፩ በእጃቸው
እንዳትወድቅ ከታላላቆች ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡
፪ በብልጽግናው
ድል እንዳያደርግህ ከባለጸጋ ጋር አትጣላ፥ ብዙዎች ስለ ወርቅ ጠፍተዋልና፤ የነገሥታትም ልቡና ድል ሆኖአልና፡፡
፫ ከተናጋሪ
ሰውም ጋር አትከራከር፤ ያለዚያ በእሳት ላይ እንጨት መጨመርህ ነው፡፡
፬ እናትና
አባትህን እንዳታዋርድ፥ከአላዋቂ ሰው ጋር አትሣቅ፡፡
፭ ከኀጢአት
የተመለሰውን ሰው አትንቀፈው፤እኛ ሁላችንም ኀጢአተኞች እንደሆን ዐስብ፡፡
፮ በርጅናው
ጊዜ ሰውን አታቅልለው፥ ከእኛ የማያረጅ የለምና፡፡
፯ በሞተ ሰው
ደስ አይበልህ፤ሁላችንም እንደምንሞት ዐስብ፡፡
፰ የብልሆች
ነገር አታቃልል፤ጥበብን በእነርሱ ዘንድ ታገኛለህና፥ ምሳሌያቸውን ተማር፡፡መምህራንንም አገልግል፡፡
፱ የሽማግሎችን
ምክራቸውን ጠብቅ፤ እነርሱ ከአባቶቻቸው ተአምረዋልና አንተም ከእነርሱ ተማር በኀዘንም ጊዜ የምትናገረውን ታገኛለህ የምትመልሰውንም
ታውቃለህ፡፡
፲ በእሳታቸው
እንዳትቃጠል፥ የኀጢአተኞች ሰዎችን እሳት አትጫር፡፡
፲፩ በአንደበቱ
ነገር እንዳያስትህ፥ በተሳዳቢና በጠላት ዘንድ አትከራከር፡፡
፲፪ ከአንተ
ለሚበለጽገው አታበድረው፤ ብታበድረው ግን ገንዘብህን እንዳጣህ ዕወቅ፡፡
፲፫ ከአንተ
ለሚበረታውም አትዋሰው፤ብትዋሰው ግን አንተ ራስህ እንደምትከፍል ዐስብ፡፡
፲፬ ከዳኛ ጋር
አትከራከር፥ እንደ ክብሩ መጠን ፍርድን ይለውጡለታልና፤
፲፭
እንዳይደፍርህ ከደፋር ሰው ጋራ መንገድን አትሂድ፤
እርሱ ልቡ እንደ ወደደ ያደርጋልና አንተም በእርሱ ስንፍና ትሞታለህ፡፡
፲፮ ከቊጡ ሰው
ጋር አትከራከር፤ በእርሱ ዘንድ ደም ማፍሰስ እንደ ኢምንት ነውና፥ ረዳት ወደሌለበት ቦታም ይወስድሃልና ከእርሱ ጋር ወደ ምድረ
በዳ አትውጣ፡፡
፲፯ የሰማውን
ነገር መጠበቅ አይችልምና፥ ከአላዋቂ ሰው ጋር አትማከር፡፡
፲፰ እንዴት እንደሚደርስብህ
አታውቅምና፥ ጉዳይህን በባዕድ ፊት አትናገር፡፡
፲፱ ዋጋህ
እንዳይጠፋብህ፥ ለሰው ሁሉ የልብህን ምሥጢር አትግለጥ፡፡