Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፱



ስለ ሴቶች የተሰጠ ምክር

፩ ክፉ ትምህርትን እንዳትማርብህ፥ባጠገብህ በምትተኛ ሚስትህን አታስቀናት፡፡

፪ ኀይልህን እንዳታደክምብህ፥ለሴት ልብህን አትስጣት፡፡

፫ በወጥመድዋ እንዳትያዝ የሌላ ሚስት አታባብል፡፡

፬ በዘፈኗ እንዳታስትህ ከዘፋኝ ሴት ጋር አትጫወት፡፡

፭ ፈቃዷ እንዳያስትህ  ድንግልን አትቈንጥጣት፡፡

፮ ርስትህን እንዳታጣ ለአመንዝራ ልቡናህን አትስጣት፡፡

፯ በከተማዎቹ ዙርያ አታማትር፤አደባባይዋም አያስትህ፡፡

፰ ከመልከ መልካም ሴት ዐይንህን መልስ፤ የሌላ ሚስትም ደም ግባትዋ አያስጐምጅህ፤ በሴት ደም ግባት የሳቱ ሰዎች ብዙዎች ናቸውና፤ስለዚህ ነገር ፍቅሯ እንደ እሳት ይነድዳል፡፡ 

፱ ከጐልማሳ ሚስት ጋር አትቀመጥ፤ ልቡናህን ወደ እርሷ እንዳትወስድ፥ሰውነትህንም በሞት እንዳታሰነካክል በመጠጥ ጊዜ ከእርሷ ጋር አትቀመጥ፡፡

፲ ድንገተኛ ወዳጅ እንደ እርሱ አይሆንህምና፥የቀድሞ ወዳጅህን አትተወው፡፡ አዲስ ወዳጅ ጉሽ ጠጅ ነው፤ቢከርም ግን ደስ ብሎህ ትጠጣዋለህ፡፡

፲፩ እንደሚጠፋ አታውቅምና የኃጥአን ብልጽግናቸው አያስቀናህ፡፡

፲፪ የክፉዎች ሰዎችም ተድላቸው አያስጐምጅህ፤ እስኪሞቱም ድረስ እንደማይከብሩ ዐስብ፡፡

፲፫ በሞት ከሚቀጡ መኳንንት ፈጽመህ ራቅ፤ ሰውነትህን እንዳታጠፋ የሞት ጥርጥር አያግኝህ፥ነገር ግን በወጥመድ መካከል እንደምትሄድ፥ በገደልም መካከል እንደምትመላለስ ዕወቅ፡፡

፲፬ የተቻለህን ያህል ለባልንጀራህ መልካም አድርግለት፤ ከጠቢባንም ጋር ተማከር፡፡

፲፭ ጉዳይህም ከዐዋቂዎች ጋር ይሁን፤ ነገርህ ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ ይሁንልህ፡፡

፲፮ ድሆች ሰዎች በምሳሕ ጊዜ ይኑሩ፤ክብርህም እግዚአብሔርን በመፍራት ይሁን፡፡

፲፯ ሥራው በብልሃተኛው እጅ ይከናወናል፤የአሕዛብንም አለቃ በቃሉ ጥበብ ያመሰግኑታል፡፡

፲፰ ተናጋሪ ሰው በከተማው አስፈሪ ነው፥ከቃሉም የተነሣ ፈጽሞ ይጠላል፡፡