፩ ጠቢብ ንጉሥ
ሕዝቡን ይመክራል፥ አስተዋይ ዳኛም ሥርዐትን ይሠራል፡፡
፪ ሎሌውም
እንደ ሕዝቡ አለቃ ነው፤ የከተማው ገዥ እንደሚሠራው በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ይሠራሉ፡፡
፫ አላዋቂ
ንጉሥ ሕዝቡን ያጠፋል፤ ሀገርም በሽማግሌዎች ጥበብ ትጸናለች፡፡
፬ የምድር
ግዛት በእግዚአብሔር እጅ ነው፥በጊዜውም የሚጠቅመውን ሰው በእርስዋ ላይ ያስነሣል፡፡
፭ የሰው
በረከቱ በእግዚአብሔር እጅ ነው፥ በጸሓፊም ሰውነት ክብሩን ያኖራል፡፡
በትዕቢት የሚመጣ ኅጢአት
፮ ባልንጀራህን
በሳተበት ሁሉ አትንቀፈው፥ በነቀፋህም ምንም ክፉ ነገር የምታደርግበት አይኑር፡፡
፯ ትዕቢት
በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የተጠላ ነው፥ከሁሉም ዐመፅ ትከፋለች፡፡
፰ መንግሥትም
ስለ ዐመፅና ክርክር፥ ስለ ገንዘብም፥ካንዱ ወገን ወደ ሌላ ወገን ትፈልሳለች፡፡
፱ እንግዲህ
ትቢያና ዐመድ የሚሆን፥ በሕይወትም ሳለ ሰውነቱ የሚተላ ሰው ለምን ይታበያል?
፲ የሰው
ቊስልን ባለ መድኀኒት ያድነዋል፤ንጉሥ መባል ግን ለዛሬ ብቻ ነው፥ነገም ይሞታል፡፡
፲፩ ሰውም
ከሞተ በኋላ የትል ዕድል ፋንታ ይሆናል፡፡
፲፪ የትዕቢት
መጀመርያ ሰውን ከእግዚአብሔር ትለየዋለች፤ልቡናውንም ከፈጣሪ ታርቀዋለች፡፡
፲፫ ትዕቢት
የኀጢአት መጀመርያ ናት፤ በአጸናትም ሰው ላይ ርኵሰትን ታበዛበታለች፥ ስለዚህም እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ፍዳ
ይገልጣል፥ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፡፡
፲፬
እግዚአብሔር ያለቆችን ዙፋን ያፈርሳል፤ በእነርሱም ፋንታ የዋሃንን ይሾማል፡፡
፲፭
እግዚአብሔር የአሕዛብን ሥራቸውን ነቀለ፥በእነርሱም ፋንታ ትሑታንን ተከለ፡፡
፲፮
እግዚአብሔር የአሕዛብን ሀገሮች አጠፋ፥ እስከ ምድር መሠረት ድረስ አጠፋቸው፡፡
፲፯ ፈጽሞም
አጠፋቸው፥ስም አጠራራቸውንም ከምድር ደመሰሰ፡፡
፲፰ ትዕቢት
ለሰው የተፈጠረ አይደለም፥ ቊጣና ጥፋትም ከሴት ለሚወለድ ሰው አይደለም፡፡
ክብር ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው
፲፱ የሰው ዘር
የከበረ ነው፥ የከበረ ዘር ማንነው? እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች አይደሉምን?
፳ የሰው ዘር
የጐሰቈለ ዘር ነው፥ ጐስቋላ ዘር ማንነው? የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የማይጠብቁ ሰዎች ዘር አይደለምን?
፳፩ ዳኛ
ከባልንጀራው ይልቅ የከበረ ነው፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ግን ከእርሱ ይልቅ ይከብራሉ፡፡
፳፪
ለባለጸጋውና ለከበርቴው ለድሃውም ክብራቸው እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡
፳፫ ድሃውን
ስለ ድህነቱ ይንቁት ዘንድ አይገባም፥ኀጢአተኛውንም ሰው ስለ ባለጸግነቱ ያከብሩት ዘንድ አይገባም፡፡
፳፬ ታላላቆችና
አለቆች፥ መኳንንቱም ይከብራሉ፤
ከእነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚበልጠው የለም፡፡
፳፭ ጠቢብ ቤተ
ሰብ በንጹሕ ያገለግላል፥ ዐዋቂ ሰውም አይነቅፈውም፡፡
፳፮ ሥራህን
ስትሠራ አትራቀቅ፥ በችግርህም ወራት አትመካ፡፡
፳፯ ከሚዞርና ከሚመካ፥
ምግቡንም ከማያገኝ ሰው ይልቅ፥ የሚያርስና የሚቈፍር ይሻላል፡፡
፳፰ ልጄ ሆይ፥
በየዋህነትህ ሰውነትህን ደስ አሰኛት፥የተቻለህንም ያህል አዘጋጃት፡፡
፳፱ ለራሱ
የሚነፍግ ለማን ቸር ይሆናል? ሰውነቱን የማያዘጋጃትን ሰውስ ማን ያመሰግነዋል?
፴ ድሃውን ስለ
ጥበቡ ያመሰግኑታል፥ ባለጠጋውን ግን ስለ ባለጠግነቱ ያመሰግኑታል፡፡
፴፩ በተቸገረ
ጊዜ የማያዝን ሰው፥ በተዘጋጀ ጊዜ እንዴት ደስ ይለው?