Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፫

ልጆች ለወዳጆቻቸው ማድረግ ያለባቸው ግዴታ


፩፤ ልጆቼ እኔን አባታችሁን ስሙኝ አባትን በልጆች ላይ አክብሯልና።
 
፪፤ የእናትንም አገዛዝ በልጆቿ ላይ አክብሯልና

፫፤ አባቱን የሚያከብር ልጅ ኃጢአቱይሰረይለታል። 

፬፤ እናቱንም የሚያከብራት ልጅ ድልብ እንደሚያደልብ ሰው ነው።

፭፤ አባቱን የሚያከብር ልጅ በልጁ ደስ ይለዋል በለመነበትም ቀን ጸሎቱን ፈጣሪው ይሰማዋል።
 
፮፤ አባቱን የሚያከብር ልጅ ዘመኑ ይበዛለታል።
 
፯፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ልጅ እናቱን ያሳርፋታል።
 
፰፤ ባሮቹ ለሱ እንዲገዙለት እሱም ለወለደው ላባቱ ይገዛል።
 
፱፤ ምርቃቱ ትደርስልህ ዘንድ ቢጠራህ አቤት ቢልክህ ወዴት ብለህ አባትህን አክብረው።

፲፤ ያባት ምርቃት የልጅን ቤት ያጸናልና የናት እርግማን ስር መሠረት ይነቅሳል።
 
፲፩፤ ልጅባ ባቱ ክብር የሚከብር ስለ ሆነ እናቱንም መናቅ ማቃለል ሰውን የሚያዋርደው ስለሆነ አባትህን መናቅ ማቃለል መመክያ አይሆንህምና አባትህን በመናቅ አትመካ።  

፲፪፤ ልጄ በርጅናው ጊዜ አባትህን ኧርዳው በጉልበትም ሳለ አታሳዝነው።

፲፫፤ ቢያረጅ አእምሮውንም ቢያጣ ፈቃዱን ለመፈጸም እሺ በለው ግን እንደሚቻልህ አክብረው ዋጋ በመቀበል ጊዜ አባትህን መርዳትህ አይዘናጋውምና።ባረጀ ጊዜ አባትህን አትናቀው።

፲፬፤ ስለ ኃጥአትም ፈንታ ጽድቅ ትሰራልሃለች። 

፲፭፤ በመከራህም ቀን እግዚአብሔር ያስብልሃል በረድን ጸሐይ እንዲያቀልጠው ኃጢአቶችህ እንደዚሁ ይቀልጣሉ። (ይሰረዩለታል)

፲፮፤ አባቱን የሚጠላ ሰው የተነቀፈ ነው እናቱን የሚያሳዝናት ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው።  

                                           ስለ ትሕትና

፲፯፤ ልጄ በሃይማኖትህ ላይ ሥራህ ይገለጥ እውነተኞች ሰዎችም ይወዱሃል።(ድሆች ሰዎች)  

፲፰፤ እንደገናንነትህ ብዛት መጠን እንደዚሁ ራስህን አዋርድ። በእግዚአብሔር ዘንድዋጋህን ታገኛለህ  

፲፱፤ የእግዚአብሔር ሥራው ልውጥ ነውና በተዋረዱ በጸኑ ሰዎች ላይ ይመሰገናል።
 
፳፤ ከባለጸጋ ጋር አትከራከር የታዘዝከውን አስብ እንጂ የማትችለውን ነገር አትመርምር። 

፳፩፤ ወደ እልፍኙ ግን አያገባህም።

፳፪፤ ሥላሴ ከሰው ይልቅ የገለጡህ ምሥጢር የለምና ከግብር ገብተህ ባህርየ ሥላሴን አትመርምር።

፳፫፤ ብዙ ሰዎችን መታለያቸው አሳታቸው ብዙ ሰዎችን የልቡናቸው ትዕቢት በመከራ ጣላቸው።
 
፳፬፤ ክህደትን የሚወዳት ሰው በሷ ይሞታል ፤ክፉ ልቡናም በፍጻሜ ዘመኑ ለስራ ይያዛል።

፳፭፤ ክፉ ልቡና በመከራ ይገረፋል ኃጢአተኛ ሰውም በኃጢአቶቹ ላይ ኃጢአትን ይጨምራል።

፳፮፤ ክፉ ክህደት ጸንቶባቸዋልና ለትዕቢተኞች ሰዎች ክህደት መመለስ የላትም።
 
፳፯፤ የብልህ ሰው ልቡና ምሳሌን ይተረጉማል፤ያዋቂ ሰው ዦሮም ጥበብ መስማትን ትወዳለች።

                                  ስለ ምጽዋት

፳፰፤ የምተነድ እሳትን ውኃ ያጠፋታል።እንደዚህም ሁሉ ምጽዋት ኃጢአትን ታስተሰርያለች።

፳፱፤ ምጽዋትን ለሚሰጥ ሰው በፍጻሜ ዘመኑ እግዚአብሔር ዋጋውን ያስብለታል፤ በመከራም በተሰነካከለ ጊዜ የሚድንበት ረድኤት ይገኛል።