Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፬

ለድሆችና ለችግረኞች መደረግ ስለሚገባው


፩፤ ልጄ ድኃውን ምጽዋቱን አትከልክለው፤ከሚለምንህ ከድኃውም ዓይኖችህን አትመልስ።

፪፤ የተራበች ሰውነትን አታሳዝን ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ።  

፫፤ ያዘነ ልቡናንም አታስደንግጥ የሚለምንህን ሰው አልፈኸው አትሂድ።
 
፬፤ የሚገዛልህ ቤተሰብህን አትቆጣ ከድኃም ፤ፊትህን አትመልስ።
 
፭፤ ከሚለምንህ ሰው ፊትህን አትመልስ በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ልመናውን ይሰማዋልና።
 
፮፤ ለሚረግምህ ሰው ገንዘብ ምክንያት አትስጠው።
 
፯፤ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደምትወደድ ሁን ፤ዳኞችን አገልግል ራስህንም አታኲራ። 

፰፤ ድኃውን በጆሮህ አድምጠው በየዋህነት በጎ ቃልንም መልስለት።
 
፱፤ የተበደለውንም ሰው ከሚበድለው ሰው እጅ አድነው ለሱም መፍረድ ቸል አትበል።
 
፲፤ እናት አባቱ ለሞተበትም ልጅ እንዳባቱ ሁነው ለናቱም እንደ ባሏ ቁምላት እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንደ ጻድቃን ትሆናለህ ከናትህ ይልቅ ይወድሃል።

                        ጥበብ ከፍ ከፍ እንደምታደርግ
 
፲፩፤ ጥበብስ ልጆቿን አገነነቻቸው የሚፈልጓትንም ሰዎች ትቀበላቸዋለች።
 
፲፪፤ እሷን የወደደ ሰው ሕይወቱን ወደደ ወደሷም የሚገሠግሥ ሰው ተድላ ደስታን ይጸግባል።
 
፲፫፤ የሚያጸናበትም ሰው ክብርን ይወርሳል እሷም ካደረችበት ዘንድ እግዚአብሔር ያከብራል።

፲፬፤ እሷንም የሚያገለግሉ ሰዎች እግዚአብሔርን አገልግሉት የሚወዷትንም ሰዎች እግዚአብሔር ይወዳቸዋለች።
 
፲፭፤ እሷን የሚሰማት ሰው አህዛብን ይገዛል እሷንም የሚያደምጣት ሰው ከመከራው ተዘልሎ ይኖራል።

፲፮፤ ካመንኻት ስትረዳህ ታገኛታለህ በዘመንህም ታገንሃለች ፤ታከብርሃለች።
 
፲፯፤ ጠላቱን ፈጽማ እያስፈራራችለት እያስደነገጠችለት ለመከራ እየገረፈችለት ሰውነቱን እስክታስገዛለት ድረስ እያስተማረችው በምክርም እየፈተችው ከሱ ጋራ ጸንታ ትኖር ዘንድ አስቀድማ ትሰጠዋለች።

፲፰፤ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ በረድኤት ተቀብላ ደስ ታሰኘዋለች ምክሩንም ትገልጥለታለች።
 
፲፱፤ ከሷ ወጥቶ ቢስት ግን ትለየዋለች። በሚጥለው በጠላቱም እጅ ትጥለዋለች።

፳፤ ክፉ እንደሆነ አውቀህ ጊዜውን ጊዜውን ተጠበቅ ሰውን አፍሮ ኃጢአት የሚሠራ አለና ሰውነትህን ለመጉዳት ሰው አፍረህ
 
፳፩፤ ፍርድ አታድላ እግዚአብሔርን አፍሮ ጽድቅ የሚሠራ ሰው አለና መወደድን ያገኛል።

፳፪፤ ነገሩ ለሰውነትህ እየተረዳህ የሰው ፊት አይተህ ፍርድ አታድላ ሰውነትህን እንዳታጠፋ ዘንድ አትፈር።
 
፳፫፤ ከቃሉ የተነሳ ጥበቡ ይታወቃልና ትምህርቱም ባንደበቱ ከመናገር የተነሣ ይታወቃልና የሚናገርን ሰው ቆይ እኔ ልናገር ብለህ አትከልክለው።

፳፬፤ ያልሆነ ሃይማኖት ይዘህ ስለ ሃይማኖት አትከራከር።ስለ በደልኸውም በደል ንሰሐ ገብተህ ተለማመጥ።

፳፭፤ ኃጢአትህንም መነገር አትፈር እንደ ዓባይ ያለውን ውኃ በሃምሌ በነሐሴ እሻገራለሁ አትበል።
 
፳፮፤ ለሰነፍ ሰው ራስህን አታዋርድ፤ለባለጸጋ አታድላ።

፳፯፤ ፈጣሪህ እግዚአብሔር ስላንተ ይከራከርልሃልና እስክትሞት ድረስ በሃይማኖት አትከራከር።
 
፳፰፤ ባፍህ አውታታ አትሁን ሥራህንም ቸል አትበል።
 
፳፱፤ በቤትህም እንደ አንበሳ አትገረም በውነት የሚገዛልህ ቤተ ሰብህንም አታሳዝን።
 
፴፤ በምትከፍልበት ግዜ ቀኝ እጅህን ትሰበስብ ዘንድ ወደ መሰብሰብ እንዳትመለስ እጅህን አትዘር