፩ ክፋትን
አትሥራት፤ ክፉም አያገኝህም፡፡
፪ ከበደል
ራቅ፣ እርሷም ራስዋ ካንተ ትርቃለች፡፡
፫ ሰባት እጥፍ
አድርገህ እንዳትሰበስባት፣ በኀጢአት ትልም አትዝራ፡፡
፬
ከእግዚአብሔር መንግሥትን አትለምን፤ ከንጉሥም የክብር ዙፋን
አትለምን፡፡
፭
በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ነኝ አትበል፤ በንጉሥም ዘንድ ብልህ ነኝ አትበል፡፡
፮ ዳኛ መሆንን
አትውደድ፤እነሆ፥ በደለኛውን ለመበቀል አትችልም ይሆናል፤እነሆ፥ ለባለጸጋም ታደላ ይሆናል በእውነት ሥራህም ላይ ኀጢአት
ትሠራለህ፡፡
፯ ያገርህንም
ሰው አትበድል፤ራስህንም በወገኖችህ መካከል አታስት፡፡
፰ በአንዲቱም
ቢሆን ከቅጣት አታመልጥምና፣ሁለት ኀጢአት አንድ አድርገህ አትሥራ፡፡
፱ በመባዬ
ብዛት እግዚአብሔር ኀጢአቴን ያስተሠርይልኛል፤ ለልዑል እግዚአብሔርም መባእ ከአገባሁ ይቅር ይለኛል አትበል፡፡
፲
በምትጸልይበት ጊዜ አትቸኩል፣ምጽዋት መመጽወትንም አታቃልል፡፡
፲፩
የሚያሳዝን፥ ደስ የሚያሰኝም አለና፣ባዘነ ሰው አትሳቅ፡፡
፲፪
በባልንጀራህ ሐሰትን ተግባር አታድርግ፤በወዳጅህና በባልንጀራህም ላይ እንዲህ አታድርግ፡፡
፲፫ በምንም
ሁልጊዜ ሐሰትን አትውደድ፤ፍጻሜዋ ይጐዳሃልና፡፡
፲፬
በሽማግሌዎች መካከል ብዙ ቃል አትናገር፤በአፍህ የተናገርኸውን ስእለትህን አትመልስ፥ ቃልህንም አትለውጥ፡፡
፲፭ የእጅህንም
ሥራ አታቃልል፥ፈጣሪህም የሚያበቅልልህን ቡቃያህን ቸል አትበል፡፡
፲፮ ብዙ ናቸው
ብለህ ከኀጢአተኞች ጋር አንድ አትሁን፡፡
፲፯ ጥፋት
እንደማትዘገይ ዐስብ፥ሰውነትህን ፈጽመህ አዋርዳት፥የኀጢአተኞች ፍዳቸው ትልና እሳት ነውና፡፡
፲፰ በእየነጋው
ወዳጅ አትለውጥ፤ ስለ ቀይ ወርቅ ወዳጅህን አትጣ፡፡
፲፱ መውደዷ
ከወርቅ ይወደዳልና ብልህና ደግ ሴትን አትጥላ፡፡
፳ በእውነት
በሚገዛልህ ቤተሰብህ ላይ፥ ስለ አንተ ሰውነቱን አሳልፎ በሚሰጥ በምንደኛህም
ላይ ክፉ ነገርን አታድርግ፡፡
፳፩ ብልህ ቤተ
ሰብህን እንደ ራስህ ውደደው፤ ነጻ ታወጣውም ዘንድ ተስፋ ያደረገህን ዋጋውን አታጥፋበት፡፡
፳፪ ሁልጊዜ
ከብትህን መፍቀድ አትተው፤ ከእነርሱ የሚጠቅምህን ወደ አንተ አቅርብ፡፡
፳፫ ልጆች
ቢኖሩህ ምከራቸው፤ከሕፃንነታቸው ጀምረህ ትሕትናን አስተምራቸው፡፡
፳፬ ሴቶች
ልጆችም ቢኖሩህ ጠብቃቸው፤አታስታቸው፥ አትሣቅላቸው፥ አታባብላቸውም፡፡
፳፭ ልጅህን
አቅመ ሔዋን ስታደርስ አጋባት፥ጠብቃት፥ ታላቅ ሥራንም ትፈጽማለህ፥ ከድካምም ታርፋለህ፥ነገር ግን ለብልህ ሰው አጋባት፡፡
፳፮ እንደ
ራስህ የምትወዳት ሚስት ብትኖርህ አትፋታት፡፡
፳፯ በፍጹም
ልቡናህ አባትህን አክብረው፥የእናትህንም ምጧን አትዘንጋ፡፡
፳፰ በእነርሱም
ምክንያት እንደ ተወለድህ ዐስብ፤ስላደረጉልህስ ፋንታ ምን ታደርግላቸዋለህ?
፳፱ በፍጹም
ሰውነትህ እግዚአብሔርን ፍራው፤ካህናቱንም አክብራቸው፡፡
፴ በፍጹም
ኀይልህም ፈጣሪህን ውደደው የሚያገለግሉትንም አትተዋቸው፡፡
፴፩
እግዚአብሔርን ፍራው፤ የሚያገለግለውን ካህኑንም አክብረው፤ የታዘዘልህ ዕድሉንም ስጠው፤ቀዳምያቱንና፥ ስለ ኀጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት፥ወርቹንም፥
ማታና ጧትም የሚሠዋውን መሥዋዕት፥መጀመርያ የሚወለደውንም ከብት ስጠው፡፡
፴፪ በረከትህ
ፍጽምት ትሆን ዘንድ እጅህን ለድሃ ዘርጋ፡፡
፴፫ ስጦታ
በሕያው ሁሉ ፊት ጸጋ አለው፥ ስለ ሞተ ሰውም ምጽዋት መስጠትን አትተው፡፡
፴፬ ከሚያለቅሱ
ሰዎችም አትለይ፥ከሚያለቅሱም ጋር አልቅስ፡፡
፴፭
ሕመምተኛንም ሰው መጐብኘት ቸል አትበል በዚህም ይወዱሃል፡፡
፴፮
በተናገርኸው ነገር ሁሉ ፍጻሜህን ዐስባት፥ ሁልጊዜም አትበድል፡፡