Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፮




፩ ጠላት ከምትሆን ወዳጅ ሁን፤ የክፉ ስም ፍጻሜው ስድብና ውርደት ነውና፤ ምላሱ ሁለት የሆነ ኀጢአተኛ ሰውም እንዲህ ነው፡፡

፪ ከልቡናህ ባነቃኸውም ምክር ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ አንበሳ ላምን እንደሚነጣጠቅ ሰውነትህን እንዳይነጥቋት፡፡

፫ ቅጠልህን ይበላብሃል፥ ፍሬህንም ታጣለህ፤ እንደ ደረቅ እንጨትም ይጥልሃል፡፡

፬ ክፉ ሰውነት ገንዘብ ያደረጋትን ሰው ታጠፋዋለች፤ ጠላቱንም በእርሱ የጨከነ ታደርገዋለች፡፡ እውነተኛና እውነተኛ ያልሆነ ጓደኝነት

፭ ልዝብ አንደበት ወንድማማችነትን ያበዛል፤ ልዝብ አፍም ወዳጅን ያበዛል፡፡

፮ ብዙ ሰዎች ወዳጆች ይኑርህ፤ነገር ግን ከብዙዎቹ አንዱ ምክርህን የምትገልጥለት ይሁን፡፡

፯ ወዳጅ ብታበጅ ነችግርህ ወራት ወዳጅ አብጅ ፈጥነህም እምነት አትጣልበት፤

፰ ለጥቂት ቀን የሚሆን ወረተኛ ወዳጅ አለና በመከራህም ጊዜ ከአንተ ጋር አይታገሥም፡፡

፱ ጠላት የሚሆንህና፥ የሚሰድብህ፥ ሰውረህ የሠራኸውን ኀጢአትህንም የሚገልጥብህ ወዳጅ አለ፡፡

፲ ስለ ማዕድህም የሚወድህ ወዳጅ አለ፤ እርሱም ከአንተ ጋራ አይኖርም፥ በተቸገርህም ጊዜ ይለይሃል፡፡

፲፩ ባለጸጋ በሆንህ ጊዜ እንዳንተ ይሆናል፤ ቤተ ሰብህንም ይገዛል፡፡

፲፪ ብትቸገር ግን እርሱ ባለጋራህ ይሆናል፤ እንዳታየውም ይሰወርሃል፡፡ 

፲፫ ከጠላቶችህ ራቅ፥ ወዳጆችህንም ተጠባበቃቸው፡፡

፲፬ የታመነ ወዳጅ እንደ ጸና አላባሽ አግሬ ጋሻ ነው፤እርሱን ያገኘ ሰው ድልብ አገኘ፡፡

፲፭ ለታመነ ወዳጅ ለውጥ የለውም፤ለደግነቱም ሚዛን የለውም፡፡

፲፮ የታመነ ወዳጅ የሕይወት መድኀኒት ነው፤እግዚአብሔርንም የሚፈሩ ያገኙታል፡፡

፲፯ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ወዳጅነቱን ያጸናል፤ባልንጀራው እንደ እርሱ ይሆነዋልና፡፡

                        የጥበብ በረከት
 
፲፰ ልጄ ሆይ፥ በሕፃንነትህ ጥበብን ምረጣት እስክታረጅም ድረስ ታገኛታለህ፡፡

፲፱ እንደሚያርስና እንደሚዘራ ሰው ወደ እርስዋ ሂድ፤የተባረከ ፍሬዋንም ጠብቅ፤ ስለ እርስዋ በመሥራት ጥቂት ትደክማለህ፤ ነገር ግን ፈጥነህ ፍሬዋን ትበላለህ፡፡

፳ በሰነፎች ዘንድ ፈጽማ ጐጣጕጥ ናት፤አእምሮ በሌለው ሰውም አታድርም፡፡

፳፩ የፈተና ድንጋይ አንሥተው በተሸከሙት ጊዜ እንዲከብድ፥እንደዚሁ ትከብደዋለች፤ፈጥኖም ይጥላታል:፡

፳፪ ጥበብስ እንደ ስሟ ናት፤ብዙ ሰዎችም የሚያውቋት አይደሉም፡፡

፳፫ ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ በምክሬም ጽና፤ምክሬንም አታቃልል፡፡ 

፳፬ እግሮችህን ወደ ቀንበርዋ አግባ፤ ዛንጅርዋንም ባንገትህ እሰር፡፡

፳፭ ጫንቃህን ዝቅ አድርገህ ተሸከማት፤በእግር ብረትዋም አትበሳጭ፡፡

፳፮ በፍጹም ነፍስህ ወደ እርሷ ተሰማራ፤ በፍጹም ኀይልም መንገድዋን ጠብቅ፡፡

፳፯ ፍለጋዋን ተከተል፥ ፈልጋት፥ ታገኛታለህም፡፡ያዛት፥ አትተዋትም፡፡

፳፰ በፍጻሜህም ዕረፍትን ታገኛለህ፤ደስታም ይሆንሃል፡፡

፳፱ እግር ብረትዋም እንደ ጽኑ ጋሻ ይሆንልሃል፤ዛንጅርዋም የክብር ልብስ ወደ መሆን ይመለስልሃል፡፡

፴ የዘለዓለም ወርቅ በእርሷ ዘንድ አለና፤ማሰርያዋም የሰማያዊ ሐር ጌጥ ይሆንሃል፡፡

፴፩ እንደ ክብር ልብስ ትለብሳታለህ፣ የደስታ ዘውድንም ታቀዳጅሃለች፡፡

፴፪ ልጄ ሆይ፥ ብልህ ትሆን ዘንድ ብትወድድ፣ትማርም ዘንድ በልቡናህ ብትጨክን፣

፴፫ ትሰማ ዘንድ ብትወድም ታገሥ፤ ጆሮህንም ብታዘነብል ብልህ ትሆናለህ፡፡

፴፬ በብዙ ሽማግሌዎች ዘንድ ቁም፤ ከእነርሱም ዐዋቂ ሰው ብታይ ተከተለው፡፡

፴፭ የመጽሐፉን ነገር ሁሉ ፈጥነህ ስማ፤የጥበብም ምሳሌ አይዘንጋህ፡፡

፴፮ ብልህ ሰው ብታይ ፈጥነህ ወደ እርሱ ሂድ፤እግርህም በደጃፉ መድረክ ይመላለስ፡፡

፴፯ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዐስብ፤ መጻሕፍቱንም ሁልጊዜ አንብብ፣ እርሱም ልቡናህን ያጸናዋል፤ጥበብንም ትወዳት ዘንድ ይሰጥሃል፡፡