መጽሐፈ ሲራክ ኢያሱ ሲራክ የተነገረው ነገር ይህ ነው፤ኢያሱ ማለት መድኃኒት ማለት ነው፤ሲራክ ማለት ጸሐፊ ነው፤የኢየሩሳለም ሰው የአልዓዛር ልጅ እኔ ኢያሱ ሲራክ ኢታምልክን ዘጠኙን ሕግጋት በዚህ መጽሃፍ ጻፍኩ።
የጥበብ መንገዶች
የጥበብ መንገዶች
ምዕራፍ ፩
፩፤ የጥበብ ሁሉ መገኛዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ዓለም ሳይፈጠር ጥበብ ከርሱጋር ነበረች።
፪፤ የብህር አሸዋን የዝናም ጠብታን የዘመንን ቁጥር ማን ቆጠረ።
፫፤ የሰማይን ምጥቀት የምድርን ስፋት የባህርን ጥልቀት ጥበብን ማን መርምሮ አወቃቸው።
፬፤ ጥበብ ከሁሉ አስቀድሞ ተፈጠረች።
፮፤ የጥበብ ምስጢሯ ለማን ተገለጠ።
፯፤ምክሯንስ ማን አወቀ።
፰፤ ጥበብ አንድ ነው በማያውቁት ሰዎች ዘንድ ፈጽሞ የሚያስፈራ ነው እግዚአብሔር በዙፋኑ ጸንቶ ይኖራል።
፲፤ እንደ ስጦታው ሰው በስጋዊ ሰው ሁሉ አሳደሯት ለሚወዷት ሰዎችም ሁሉ ሰጣቸው።
፲፩፤እግዚአብሔርን መፍራት ክብር ነው የሚያስመካ ተድላ ደስታም ነው ፤ተድላ ደስታ ያለው ዘውድም ነው።
፲፪፤እግዚአብሔርን መፍራት የልብተድላ ደስታ ነው ተድላ ደስታን ይሰጣል፤ደስም ያሰኛል በህይወት የሚኖሩበትን ዘመን ያበዛል።
፲፬፤ የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ከናታቸው ማህጸን ከተወለዱ በኋላ ለምዕመናን ታሰራለች።
፲፭፤ ከጥንት ጀምሮ ለሰው ተፈጠረች ከልጆቻቸው ጋራ ጸንታ ልትኖር ታመነች።
፲፮፤ጥበብን መጥገብ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ምሥጢሩን ትገልጥላቸዋለች።
፲፯፤በመምህራን ጉባኤ ተድላ ደስታ መልቷል በቦታዋም ትምህርት አለ።
፲፰፤ የጥበብ ዘውዷ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ፍቅር አንድነትን ያመጣታል ፈጽሞ ያድናል።
፳፤ የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ሥራቷም በህይወት የሚኖሩበትን ዘመን ያበዛል።
፳፩፤በተቆጣ ግዜ መከራ ይመጣበታልና ቍጡ ዓመጸኛ ሰው አይጸድቅም።
፳፪፤ጊዜዋን እስክታሳልፍ ድረስ ነገርህን ቍጣን ታገሳት ኋላ ደስ ታሰኝሃለች።
፳፫፤ጊዜውን እስክታገኝ ድረስ ነገርህን ሠውር ብዙ ሰዎች ጥበብህን ይናገራሉ።
፳፬፤በመምራን ጉባኤ መስለው የሚያስተምሩት ትምህርት አለ።ኃጢአተኛ ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን ይጸየፈዋል።
፳፭፤ጥበብን ከወደድካት ትእዛዙን ጠብቅ ጥበብም ጥበብን ይሰጥሃል።
፳፮፤ጥበብ ይሉሃል እውቀት ይሉሃል እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ፈቃዱም ምግባርና ሃይማኖት ነው።
፳፯፤እግዚአብሔርን መፍራት አትዘንጋ።
፳፰፤እየተጠራጠርህ እግዚአብሔርን ሁለት ልብ ሆነህ አታገልግለው።
፳፱፤በሰው አፍ አትነስ ከንፈሮችህም ክፉ ነገር ከመናገር ጠብቅ።
፴፤እንዳትጎሰቁል ሰውነትህም በመከራ እንዳትወድቅ ራስህን አታኲራ። እግዚአብሔርም ሠውረህ የሠራኸው ኃጢአትህን ይገልጥብሃል።እግዚአብሔርን በመፍራት አልመጣህምና በብዙ ሰዎች መካከል በመከራ ይጥልሃል።በልብህም ክዳት አለ።