Sunday, October 6, 2013
ምዕራፍ ፵፪
፩. ነገር ግን ስለዚህ ነገር አትፈር እግዚአብሔር በፍርድ አታድሉ ስላለ በደል እንዳይሆንብህ ለሰው ፊት አይተህ አታድላ፡፡
፪. ይሙት በቃውን ይድን በቃ ብለህ እንዳትፈርድ ስለ ፍርድህና ስለ ሥራትህም አትፈር፡፡
፫. ካሽሙርህ ጋር ገንዘብህን በተቆጣጠርህ ጊዜ አትፈር ስለ ርስትህና ስለ ዋጋህም አትፈር፡፡
፬. ስለ ላዳንና ስለሚዛንም ጥቂትም ብዙም ቢሆን ስለ ገንዘብህም አትፈር፡፡
፭. ስለሚረባህ ስለሚጠቅምህም ሁሉ አትፈር ልጆችህንም ስለማስተማር አትፈር ክፉ ባሪያህንም ጎን ጎኑን ግጠበው፡፡
፮. ገንዘብ የምታባክን ሴት ቁልፍ መያዝ ያማረ ነው አገባቡም በቁጥር ከሆነ ዘንድ በቁጥር አኑር፡፡
፯. የምትሰራውን ሁሉ በቁጥር በሚዛንና በላዳን አድርግ ያወጣህውና ያገባህው ያነሳህው የሰጠህው ሁሉ በደብዳቤ ይሁንህ፡፡
፰. ሰነፍን ሰው አእምሮ የሌለውንም ሰው ባረጀ ጊዜ ወደ ዝሙት የሚሄድ ሽማግሌንም ስለመምከር አትፈር ይህን ያደረግህው እንደሆነ በሰው ሁሉ ዘንድ በውነት ፈጽመህ አዋቂ ትሆናለህ፡፡
፱. ሴት ልጅ ላባቷ የተሰወረ ቁርጥማት ናት እሷንም ማሰብ እንቅልፍ ያሳጣዋል በሕጻንነቷ ጀምረህ እስክታድግ ድረስ ጠብቃት ሳትባልግም አጋባት፡፡
፲. ካገባችም በኋላ መካን እንዳትሆን ጸልይላት፡፡
፲፩. የጠላትህ መዘባበቻ እንዳታደርግህ የማታፍር ልጅን አጽንተህ ጠብቃት በብዙ ሰዎች መካከልም እንዳታሳፍርህ ለወገኖችህ ወገን ለወዳጆችህ ንገር፡፡
፲፪. ሰውን ሁሉ ስለመልኩ አታድላለት ወደ ሴቶችም መካከል አታግባው፡፡
፲፫. ከልብስ ብል ይገኛል ኃጢአትም ሁሉ ከሴቶች ይገኛል፡፡
፲፬. ከሴት ቸርነት የወንድ ንፍገት ይሻላል ውሽማዋንና ባሏን የምታቃና ሴት አፍረት ናት፡፡
፲፭. እንግዴህ ወዲህ ግን የእግዚአብሔርን ስራ አስባለሁ ያየሁትንም እናገራለሁ ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረዋልና፡፡
፲፮. ጸሐይ ያበራል ሁሉንም ያሳያል የእግዚአብሔርም ብርሃኑ በሁሉም ምሉ ነው፡፡
፲፯. ታምራቱን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ እግዚአብሔር ለወዳጆች ብርሃንን አልፈጠረምን ይሉ ፍጥረትን ያጸና ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ነው ሁሉም በጌትነቱ ጸንቶ ይኖራል፡፡
፲፰. ልብንና ጥልቅንም መርምሮ ያውቃቸዋል ምክራቸውንም ሁሉ ያውቃል እግዚአብሔር የልቡና ሃሳብን ሁሉ ያውቃልየዓለም ምልክት የሚሆን ጨረቃንም ሁሉ እይ፡፡
፲፱. ያለፈውንም የሚመጣውን እሱ ይገራል የተሰወረውንም ምስጢር ይገልጣል
፳. ከእግዚአብሔር ምክር ሁሉ የሚያመልጥ የለም ከነገሩ ሁሉ አንዲት ቃል ስንኳ የሚሰወረው የለም፡፡
፳፩. የመለኮቱ ክብር ለስጋው ጌጥ አደረገ ይህቺም ቃል አለም ሳይፈጠር የነበረች ናት ለዘለዓለሙም ጸንታ ትኖራለች አትጨምርም አትጎድልም አንድ መከርን ስንኳ አልፈለገም፡፡
፳፪. ፍጥረቱ ሁሉ ፈጽሞ ያማረ ነው ብርሃንም እንደ መሆኑ ሊያዩት ያማረ ነው፡፡
፳፫. ይህ ሁሉ ለዘላለሙ በሕይወት ይኖራል የሚወዱትን ልመናቸውን ሁሉ ይሰማል፡፡
፳፬. አንዱም ካንዱ ጋራ ሁለት ሁለት ሆኖ ተፈጠረ ምንም ምንም ነጠላ አድርጎ የፈጠረው የለም፡፡
፳፭. ለመባዛት አንዱን ካንዱ ጋራ አጸናው ፍጥረቱን ከማየት ማን ይጠግባል፡፡