Sunday, October 6, 2013
ምዕራፍ ፵፩
፩. በሕይወት ሳለ በሁሉ ተዘጋጅቶ ሳለ ኃይልም ላለው ለመብላት ሆዱም ተከፍቶ ሳለ በሰው ላይ በመጣህ ጊዜ ሞት ስም አጠራርህ ምን ይከፋ፡፡
፪. ገንዘብ ሳይኖረው ፈጽሞም ባረጀ የሚያደርገውም ምንም ምን ሳይኖረው የሚያውቀውም ሳይኖር በድሃ ሰው ላይ በመጣህ ጊዜ ሞት ስም አጠራርህ ምን ያምር፡፡
፫. የሞትን ፍርድ አትፍራ የእግዚአብሔር ፍርድ ሞት በሰው ሁሉ ላይ አለና ካንተ አስቀድሞ የነበሩትን
፬. ካንተም በኋላ የሚነሱትን አስባቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሞትን ለምን ትነቅፋለህ ሺ ዘመንም ብትኖር ሕይወት የባሕሪየ ነው ብለህ ከሞት ጋር ክርክር የለህም፡፡
፭. የኃጢአተኞች ሰዎች ልጆች ጎስቋሎች ልጆችን ይሆናሉ የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጉ ሰዎችም ቤታቸው ይፈርሳል፡፡
፮. የኃጢአተኞች ልጆች ራሳቸውን የጣሉ ኃጢአታቸውም ከልጆቻቸው ጋራ አደገ፡፡
፯. ስለሱ ይዋረዳሉና የኃጢአተኛ አባት ልጆች ይጎሰቁላሉ፡፡
፰. የእግዚአብሔርን ሕግ ላፈረሳችሁ ኃጢአተኞች ሰዎች ወዮላችሁ፡፡
፱. ብትወልዱም ለርግማን ትወልዳላችሁ፡፡
፲. ሰው ሁሉ ከምድር ተፈጠረ ዳግመኛም በሞት መመለሳቸው ወደ ምድር ነው ኃጢአተኞችም ሰዎች ከርግማን ወደ ሞት ይሄዳሉ፡፡
፲፩. የሰው ልቡናው በግዘፉ ጸንቶ ይኖራል የኃጢአተኞች ሰዎችም ስማቸው ይጠፋል፡፡
፲፪. ስምህን ታስጠራ ዘንድ በጎ ስምን አስብ ወርቅ ድልብ እሱ ብቻ ይቀርሃል፡፡
፲፫. በዘመንህ ቁጥር በተድላ በደስታ መኖር ያማረ ነው እሱ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኖርልሃልና በጎ ስም ይሻላል፡፡
፲፬. ጥበብ ግን ልጆቿን በተድላ በደስታ ትጠብቃቸዋለች የተሰወረ ጥበብ የማይታይ ድልብ የሁለቱ ጥቅማቸው ምንድነው፡፡
፲፭. ጥበብን ከሚሠውር ሰው ስንፍናውን የሚሸሽግ ሰው ይሻላል፡፡
፲፮. እንግዴህ ጥበቤንና ቃሌን እፈሩ በጎ ነገሬን የሚያፍር ሰው በበጎ ረድኤት ይጠበቃል በሁሉ ሊማከሩ ይገባል ነገር ግን ሁሉ የታመነ አይደለም፡፡
፲፯. ልጅ እንወልዳለን ብለው በዝሙት መኖር ለናትና ላባት እፍረት ነው ለመኳንንትና ለአለቃም አሰት መፍረድ አይገባም፡፡
፲፰. ለሹምና ለዳኛ ቃል መለወጥ አይገባም ለማኅበርና ለሕዝብም ከሕግ ወጥቶ መሳት አፍረት ነው ካሽሙርህና ከወዳጅህ ጋራ መከዳዳት አይገባም፡፡
፲፱. ለእንግዳ ካደረበት ቦታ ሰርቆ መሄድ አፍረት ነው የሌላ ሰው እህል ለመብላት ጥቂት እህል ይዞ መቅረብ አይገባም ከባልንጀራህ ገንዘብና ካደራ ገንዘብ መስረቅ አፍረት ነው፡፡
፳. የሚጠራህን ሰው ቸል ማለት አይገባም የጎልማሳ ሚስትንም ማቃጠር አይገባም፡፡
፳፩. በመከራው ጊዜ ባልንጀራህን ቸል ማለት አፍረት ነው ለሌላ ገንዘብም መሳሳት አይገባም፡፡ የጎልማሳ ሚስት ማነጋገር አይገባም እሰጥሻለሁ ብለህ አትካዳት፡፡
፳፪. ልጅዋንም አታባብላት ወደ መኝታዋም አትቅረብ ካሰብኌው በኋላ በወዳጅህ መለገድ አይገባም የወዳጅህን ምስጢር ማውጣት አፍረት ነው፡፡
፳፫. ይህንን ከጠበቅህ በውነት እግዚአብሔርን የሚያፍር ትሆናለህ በሰውም ሁሉ ዘንድ መወደድን ታገኛለህ፡፡