Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፪



1  በጎ ሥራ በሠራህ ጊዜ የበጎነትህን ዋጋ ታገኝ ዘንድ በጎ ስራ የምትሰራለትን ዕወቅ።

2 ለጻድቅ በጎ አድርግ ዋጋህንም ታገኛለህ በእርሱ ዘንድ ባታገኘው በፈጣሪው ዘንድ ታገኛለህ። 

3 ኀጢአትን በሚሠራና ምጽዋትን በማይመ ጸውት ዘንድ በጎ ሥራ የለም።

4 ኀጢአተኛ እንዳይወስድህ ለጻድቁ ስጥ። 

5 ለደሃ መልካም ነገር አድርግ። ለክፉ ግን አትስጥ። እርሱ እንዳይወስድብህና በገንዘብህ ድል እንዳያደርግህ እንጀራህን ከልክለው። በጎ ነገር ስላደረግህለት ፋንታ በእርሱ ዘንድ ክፋትን እጥፍ ሆና ታገኛታለህና።

6 እግዚአብሔር ኀጢአተኞች ሰዎችን ይጠላቸዋል፤ ክፉ ሰዎችንም ይበቀላቸዋልና። 

7 ለኀጢአተኛ ከምትሰጥ ለጻድቅ ስጥ፤ በደስታህ ጊዜ ወዳጅህ አያምልጥህ።

8 በመከራህም ጊዜ ጠላትህ አይውረስህ። 

9 ደስታህ ጠላቶችህን ያሳዝናቸዋል። ችግርህም ወዳጆችህን አስወጥቶ ይሰዳቸዋል።

10 የልቡናው ክፋት እንደ ብረት ዝገት ነውና፤ ጠላትህን ፈጽመህ አትመነው።

11 በተቸገርህም ጊዜ እያመሰገነ ያገለግልሃል፤ ሰውነትህን አጽናት፤ ከእርሱም ተጠበቅ፤ እንደዛገ መስታወት ትሆንበታለህ፤ ፈጽሞም አይችልህም። 

12 እንዳይጎዳህ በአጠገብህ አታቁመው፥ በቦታህም አይቀመጥ፤ ሹመትህን እንዳይወስድህ በቀኝህ አታስቀምጠው። በመጨረሻም ቃሌን ታውቀው ዘንድ አለህ፥ ምክሬንም ታስበዋለህ። 

13 በእባብ ለተነደፈ አስማተኛ፥ ወደ ክፉ አውሬ ለቀረበ ሁሉ ማን ያዝንለታል?

14 ከኀጢአተኛም ሰው ጋር የሚሄድ በኀጢአቱ የሚተባበርም እንዲሁ ነው።

15 ጠላትህ ከአንተጋ አንድ ጊዜ ይቆማል፥ ነገር ግን እስክትመለስ ድረስ አታየውም፥ ከአንተም ጋር አይታገሥም። 

16 ጠላትህ በከንፈሩ ቃሉን ያጣፍጥልሃል። በልቡ ግን በጉድጓድ ውስጥ ይጥልህ ዘንድ ይመክራል። ጠላትህ በዐይኑ ያለቅስልሃል፥ ካሳተህ በኋላ ግን ከደምህ አይጠግብም።

17 ብትቸገርም ከሁሉ አስቀድሞ በፊትህ ታገኘዋለህ፤ እንደሚረዳህም ከጫማህ በታች ራሱን ዝቅ ያደርጋል። 

18 በእጁ ያጨበጭባል፤ ራሱንም ይነቀንቃል፤ ከዚህ በኋላ ግን ፊቱን መልሶ ይጠቃቀስብሃል።