Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፫




ከጓደኛ ስለ መጠበቅ

1 አደሮ ማር የዳሰሰ ሰው በእርሱ ይያዛል፤ ትዕቢተኛ ሰውንም ወዳጅ ያደረገ እንደ እርሱ ይሆናል። 

2 የከበደ ሸክምን አንስተህ በራስህ አትሸከም፤ ገንዘብህንም ከሚበረታብህና ከባለጸጋ ገንዘብ ጋራ አትጨምር፥ የሸክላ ድስት ከብረት ድስት ጋር በየት አንድ ይሆናል? እርስዋ መትታ እርስዋ ትጮሃለችና፥ እርስዋም ትሰብራለችና። 

3 እንደዚሁ ሁሉ ባለ ጸጋ እርሱ ይበድላል፥ እርሱም ይቈጣል፤ ደሃ ግን እርሱ ይገፋል እርሱም ይለማመጣል። 

4 የምትጠቅመው ነገር ቢኖር ወደ እርሱ ያቀርብሃል፤ ብትቸገር ግን ከዚያ በኋላ አያይህም።

5 ገንዘብ ቢኖርህ ከአንተ ጋራ አንድ ይሆናል፥ ያንተን ይጨርስልሃል፤ ዳግመኛም አያመሰግንህም።

6 አንተን የሚፈልግበት ግዳጅ ቢኖረው ያባብልሃል፤ ብዙም ተስፋ ይሰጥሃል፤ ይስቅልሃል፤ በጎ ነገርም ይናገርሃል፤ ምን ትፈልጋለህም ይልሃል። 

7 በመብሉም ይሸነግልሃል፤ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ፥ ሦስት ጊዜም ያስትሃል፤ ከዚህም በኋላ እንደማይሰማህ ወደ ኋላ ይመለሳል፤ ቢያይህም ይስቅብሃል፤ ራሱንም ይነቀንቅብሃል።

8 እንዳያስትህና እንዳያታልልህ ከእንዲህ ያለ ሰው ተጠበቅ፥ በደስታህም መካከል ኀዘን አታግባ።

9 ባለጸጋ ያዘዘህን ለጊዜው እሽ በለው፥ ቢጠራህም እምቢ አትበለው፤ ፈጽሞም ይወድሃል።

10 አትራቅ አትሳትም፥ ነገር ግን እንዳይዘነጋህ ፈጽመህ አትራቀው።

11 ከእርሱ ጋር ነገርን አታብዛ፤ በነገሩ ብዛት ይፈትንሃልና፤ ከአንተም ጋራ የሚስቅ መስሎ ይመረ ምርሃልና በነገሩ ብዛት አትመነው።

12 መታሰሩና ጥፋቱ አያሳዝነውምና የባልንጀራውን ምስጢር ለሚያወጣ ሰው ይቅርታ የለውም።

13 ከገዳይህ ጋር ትሄዳለህና እወቅ፤ አጥብቀህም ተጠበቅ። 

14 ከብት ሁሉ ዘመዱን ይወድዳል፤ ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ይወድዳል።

15 ፍጥረቱ ሁሉ እንደ እርሱ ካለ ፍጥረት ጋራ አንድ ይሆናል፤ ሰውም የሚመስለውን ይከተላል።

16 ተኩላ ከበግ ጋር በየት ወዳጅ ይሆናል? ኀጢአተኛ ሰውም ከጻድቅ ሰው ጋራ እንዲሁ ነው።

17 ውሾች ከጅቦች ጋር ማን ያስማማቸዋል? ደሃውንስ ከባለጸጋው ጋራ ማን ወዳጅ ያደርገዋል? 

18 የሜዳ አህዮች የአንበሶች አደን ናቸው፤ እንደዚሁም ሁሉ ባለጸጋው ድሃውን ይቀማዋል።

19 ትዕቢተኛ ሰው ራሱን የሚያዋርደውን ሰው ይጸየፈዋል፤ እንዲሁም ሁሉ ባለጸጋው ድሃውን ይጸየፈዋል። 

20 ባለጸጋ ቢፍገመገም ወዳጆቹ ይደግፉታል። ድሃ ግን ቢወድቅ ባልንጀሮቹ ይረግጡታል።

21 ባለጸጋ ቢያድጠው ብዙ ሰዎች ያነሱታል። ክፉ ቢናገርም ነገሩን ያቀኑለታል፤ ድሃ ግን ቢስት ይረግሙታል፤ በጎ ነገርም ቢናገር አያደምጡትም።

22 ባለጸጋ ቢናገር ሁሉ ዝም ይላል፤ ቃሉንም ያደንቁለታል፥ ነገሩንም እስከ ደመና ያደርሱለታል፤ ድሃ ግን ምንም በጎ ነገር ቢናገር ይህ ምንድን ነው? ይሉታል፤ ቢሰነካከልም ያዳፉታል። 

23 ኀጢአት ሳትሰራ ባለጸግነት መልካም ነው፤ ኃጥእ ድህነቱን ባፉ ያክፋፋታል። 

24 ደስ ቢለው ቢያዝንም የሰው ልቡ ፊቱን ይለውጠዋል። 

25 ደስ ያለው ልቡና ምልክቱ ብሩህ ገጽ ነው፥ ደክመህ የጥበብን ምክር ታገኛለህ።