Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፩




1 ድሃ በጥበቡ ይከብራል፤ በመኳንንትም መካከል ይቀመጣል።

2 ስለ መልከ መልካምነቱ ለሰው አታድላ። ስለ መልከ ጥፉነቱም ሰውን አትናቀው። 

3 ንብ ከወፎች ሁሉ ታንሳለች፤ ማርዋ ግን ከሁሉ ይጣፍጣል። 

4 በልብስህ ጌጥ አትታበይ። በከበርህበትም ወራት ራስህን አታኩራ። የእግዚአብሔር ሥራው ልዩ ጥበቡም ከሰው የተሰወረ ነውና። 

5 በምድር የወደቁ መኳንንት ብዙ ናቸው፤ ዘውድ የተቀዳጀ ባሕታዊም አለ። 

6 ፈጽመው የተዋረዱ መኳንንት ብዙ ናቸው።

7 ሳትመረምር አትንቀፍ፤ አስቀድመህ ተረዳ፥ በኋላም ትቈጣለህ። 

8 ሳትሰማ አትመልስ፤ በሌላውም ነገር ውስጥ አትግባ። 
 
9 ግዳጅህም ባልሆነ ነገር አትጨነቅ፤ ከኀጢአተኞች ጋርም በፍርድ አትቀመጥ። 

10 ልጄ ሆይ፥ ሥራህን አታብዛ፤ ብታበዛ ትከብር ዘንድ አያሠለጥንህምና፤ ብትሮጥ አታመልጥም፥ ብትከተልም አታገኝም።

11 የሚቸኩልና የሚሠራ፥ የሚደክምም አለ፤ ነገር ግን እጅግ ይቸገራል።

12 ደክሞ ሳለም የማይለምን፥ ምንም ማድረግ ሳይችል የሚገዛ አለ፤ ምንም ቢጸና ፈጽሞ የሚቸገር አለ።

13 እግዚአብሔር ግን በመልካም ዐይን ቢያየው ከችግሩ ያነሣዋል። ከፍ ከፍ ያደርገዋል፥ ያከብረዋል፥ ብዙ ሰዎችም ያደንቁታል።

14 መልካምና ክፉ፥ ሕይወትና ሞት፤ ድህነትና ብልጽግና ከእግዚአብሔር ዘንድ ናቸው።

15 ጥበብ፣ ማስተዋልና ሕግን ማወቅ ፍቅርና መልካም ሥራን መሥራት ከእግዚአብሄር ዘንድ ይመጣሉ።

16 ስሕተትና ጨለማ ከመወለዳቸው ጀምሮ ከኃጥኣን ጋር ኖረዋል። ክፋትም በእርሱ ደስ ከሚሰኙት ጋር አብሮ ያድጋል።

17 የእግዚአብሄር ጸጋው ጻድቃንን ትጠብቀዋለች። ፈቃዱንም ለዘለዓለም ደስ ታሰኛለች። 

18 እየነፈገ በንፍገቱ ብዛት የሚከብር ሰው አለ። በእርስዋም ደስታውን ይፈጽምባታል። 

19 ያርፍ ዘንድ ተስፋ ባደረገ ጊዜ እበላለሁ እጠጣለሁ፥ እንግዲህስ ደስ ይለኛል፥ በቃኝም ባለ ጊዜ የሚሞትባትን ጊዜ አያውቅም፤ ገንዘቡንም ሁሉ ለባዕድ ትቶ እርሱ ይሞታል። 

20 በቃል ኪዳንህ ቁም፤ በእርሱም ተማር፤ በስራህ ሸምግል።
 
21 የኀጢአተኞች ሥራቸው አያስጎምጅህ፥ በእግዚአብሔር እመን፥ ድካምህንም ተስፋ አድርግ፥ ሁሉ በአንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀሊል ነውና፥ ድሃውንም ድንገት ያከብረዋልና። 22 የእግዚአብሔር በረከት ለጻድቃን ዋጋቸው ናት። የጻድቅም በረከቱ ትበዛለች።
 
23 የአገልግሎቴ ትርፍ ምንድነው? ከእንግዲህስ የማገኘው መልካም ነገር ምንድነው ? አትበል።

24 እንግዲህስ በቃኝ፥ ከእንግዲህም ወዲያ አልቸገርም አትበል። 

25 በመልካም ቀን ጊዜ ክፉ ይረሳል፤ በክፉም ቀን ጊዜ መልካም ይረሳል። 

26 የሞት ቀን በእግዚአብሔር ዘንድ ቀሊል ነው። ለሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋልና።

27 በክፉ ቀን ጥጋብ ያቀናጣል፤ የሰውም ሥራው በፍጻሜ ዘመኑ ይታወቃል።

28 ፍጻሜውን ሳታይ ሰውን ብጹዕ አትበለው የሰው አኗኗሩ በልጆቹ ይገለጣል። 

                       ጓደኛን ስለመምረጥ

29 ተንኰለኛ ብዙ ይተነኰልብሃልና ያገኘኸውን ሰው ሁሉ ወደ ቤትህ አታስገባ። 

30 ቆቅ በወጥመድ ይያዛል፥ የትዕቢተኛ ሰውም ልቡ እንደዚሁ ነው፤ መከራውንም እንደ ጉበኛ ይመለከታል። 

31 ተንኰለኛ ሰው በበጐ ፋንታ ክፉ ነገርን ይከፍልሃል፤ ሳይኖርብህ ነውርን ያወጣብሃል። 

32 በእሳት ትንታግ ብዛት ፍሙ ይበዛል፤ ኀጢአተኛ ሰውም ሰውነቱን ያጠፋታል። 

33 ክፉ ነገርን ይሠራብሃልና፥ ሁልጊዜ ስድብን እንዳያደርግብህ ከክፉ ሰው ተጠበቅ። 

34 ባዕድ ሰውን ከአንተ ጋር ብታሳድር ያውክሃል፤ ይወነጅልሃል፥ ከገንዘብህም ይለይሃል።