Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፳፭




፩ በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ያማርሁ ሆንሁ በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ያማርሁ ሆኜ ቆምሁ፥ እነዚህም በአንድ ልብ የሚተባበሩ ወንድማማቾች፥ የባልንጀሮች ፍቅር፥ የባልና ሚስትም ስምምነት ናቸው፡፡

፪ ሦስት ዐይነት ሰዎች ሰውነቴ ፈጽማ ጠላቻቸው፤-ኑሯቸውም እጅግ አበሳጨኝ፤ እነዚህም ትዕቢተኛ ድሃ፥ ንፉግ ባለጸጋና አእምሮ የሌለው ሴሰኛ ሽማግሌ ናቸው፡፡

፫ ከሕፃንነትህ ጀምረህ ያልተመከርህ፥ በእርጅናህ ጊዜ እንዴት ብልህ ትሆናለህ?

፬ ሺበት ፍርድ ሊሰጥ ይገባዋል፤ ሽማግሎችም መምከር ይገባቸዋል፡፡

፭ ለሽማግሎችም ጥበብ ይገባቸዋል፤ለታላላቅ ሰዎችም ጥበብን መማር ይገባቸዋል፡፡

፮ የትምህርት ብዛት የሽማግሎች ዘውዳቸው ነው፤መመኪያቸውም እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡

፯ በልቤ ያደነቅኋቸው ዘጠኝ ናቸው፤ዐሥረኛውን ግን በቃሌ እናገራለሁ፤እነርሱም በልጆቹ ደስ የሚለው ሰው፥በሕይወቱም ሳለ የጠላቱን ውድቀት የሚያይ ሰው ናቸው፡፡

፰ ልባም ሴትን ያገባ ብፁዕ ነው፤በአንደበቱም ያልሳተ ሰው ብፁዕ ነው፤ከእርሱ ላነሰ ሰው ያላደረ ብፁዕ ነው፤

፱ ዕውቀትና ጥበብን ያገኛት ሰው፥የሚታዘዝላትንም ያገኘ ሰው ብፁዕ ነው፡፡

፲ ጥበብን ያገኘ ሰው እንዴት ታላቅ ነው!ነገር ግን እግዚአብሔርን መፍራት ይህን ይበልጠዋል፡፡

፲፩ እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ትበልጣለች፡፡ 

፲፪ እርሷንም የጠበቀ ሰውን የሚመስለው የለም፡፡

፲፫ ከቊስል ሁሉ ይልቅ የልብ ቊስል ይከፋል፤ ከክፋትም ሁሉ የሴት ክፋት ትከፋለች፡፡
 
፲፬ በሁሉም ብትወድቅ በጠላትህ እጅ አትውደቅ፤ ሁሉ ቢበቀልህ ጠላትህ አይበቀልህ፡፡
 
፲፭ ከእባብ ራስ የሚከፋ ራስ የለም፤ ከጠላትም ቂም የሚከፋ ቂም የለም፡፡

       የክፉ ሴት ተግባር

፲፮ ከክፉ ሴት ጋራ ከምትኖር፥ ከአንበሶችና ከምድር አውሬዎች ጋር መኖር ይሻላል፡፡
 
፲፯ ክፋትዋ መልኳን ይለውጠዋል፤ ፊትዋንም እንደ ድብ መልክ ያጠቊረዋል፡፡ 
 
፲፰ ባሏንም በባልንጀሮቹ መካከል ይንቁታል፤ መራራ ኀዘንንም ያሳዝኑታል፤ አስጨንቀውም ይይዙታል፡፡

፲፱ ክፋት ሁሉ ከሴት ክፋት ታንሳለች፤ እርስዋም ወደ ኀጢአት ዕድል ታደርሳለች፡፡
 
፳ የአሸዋ ዐቀበት የሽማግሌዎችን እግራቸውን እንደሚያደክም፥ እንዲሁ ቀባጣሪ ሴት የዋህ ባልን ታደክመዋለች፡፡
 
፳፩ የሴት መልኳ አያስትህ፤ሀብቷም አያስጐምጅህ፡፡ መቅሰፍትና ጥፋት ጽኑ ውርደትም ናትና፤

፳፪ ሴት ባሏን ብትመግበው፥ ቊጣን፥ አለማክበርንና ብዙ ዘለፋን የተሞላች ትሆናለች፡፡
 
፳፫ ለልብ ቊስል ናት፥ ለፊትም ጥቁረት ናት፥ ለነፍስም ኀዘን ናት፤ እንዲሁ ባሏን የማታከብር ሴት እንደ ሽባ እጅና ልምሾ እንደ ሆነ እግር ናት፡፡
 
፳፬ በመጀመርያም ኀጢአት ከሴት ተገኘች፤ በእርስዋም ምክንያት ሁላችን እንሞታለን፡፡

፳፭ ለውኃ መፍሰሻ አታብጅለት ለሴትም የልብህን ምሥጢር አታውጣላት፡፡

፳፮ እንደ ጠባይህ ካልሆነች ፍታት፤ ከሰውነትህም ለያት፡፡