Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፳፬



                    የጥበብ ክብር

1. ጥበብ ራሷን ታመሰግናለች በአህዛብም መካከል ትመካለች፤

2. በልዑልም ጉባኤ ትነገራለች በኃይሉም ፊት ትመካለች፤ 

3. አንዲህም አለች እኔ ከልዑል አፍ ወጣሁ ምድርንም እንደጉም ሸፈንኋት፤

4. እኔ በሰማይ ኖርሁ ዙፋኔንም በደመና አምድ ላይ ዘረጋሁ፤ 5. ብቻዬንም በሰማይ ዳርቻ ዞርሁ በውቅያኖስ መካከልም ተመላለስሁ 

6. በባህርም ማዕበል ላይ፣ በየብስም መካከል ሁሉ በህዝብና በአህዛቡ ሁሉ ጥሪትን አደረግሁ፡፡ 

7. ከዚህም ሁሉ በኋላ እረፍትን ፈለግሁ እንግዲህ በማን እርስት አድራለሁ? 

8. ከዚህም በኋላ ሁሉን የፈጠረ አዘዘኝ፤ ፈጣሪም ማደሪያዬን አዘጋጀልኝ እንዲህም አለኝ በያዕቆብ እደሪ እርስትሽም በእስራኤል ይሁን፡፡ 

9. ዓለም ሳይፈጠር ወለደኝ ለዘላለሙም ከእርሱ አልለይም፤

10. በተቀደሰ ማደሪያውም በፊቱ አገለገልሁ በጽዮንም አደርሁ፤ 

11. እንዲሁም በተወደደችው ከተማ አረፍሁ ግዛቴም ባስገዛን በኢየሩሳሌም ነበር፡፡

12. በእግዚአብሔር ርስት እድል ፋንታ በከበረ ህዝብ መካከል ስር ሰደድሁ፤

13. በሊባኖስ እንዳለ ዝግባ ከፍ ከፍ አልሁ፤ በኤርሞን ተራራ እንዳለ ዋንዛም ገነንሁ፡፡

14. በውሃ ዳር እንዳለ ዘንባባ ረዘምሁ፤ በኢያሪኮ እንዳለ ጽጌረዳ በምድረበዳ እንዳለች እንዳማረች የዘይት እንጨትም መዓዛዬ የተወደደ ሆነ፤ እንደዋርካ ዛፍም ገነንሁ፡፡

15. መዓዛዬም እንደቀናንሞስና እንደደርሶኒ ሽቱ የተወደደ ሆነ፤ መዓዛዬም እንዳማረ የሽቱ መዓዛ ሆነ፤ እንደልባንጃ እና እንደ ጥርኝ ሰጡቃጤ እንደሚባል ሽቱ በደብተራ ኦሪት እንዳለ እንደ ደነጭ እጣን መዓዛ የተወደደ ሆነ፡፡ 

16. ቅርንጫፎች እንደ ቡጥም ረዘሙ፤ ቅርንጫፎችም የክብርና የጌትነት ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ 

17. እኔስ እንደተወደደ የወይን ሐረግ መወደድን አስገኘሁ፤ 

18. አበባዬም የክብርና የባለጸግነት ፍሬ ነው፡፡

19. የምትወዱኝ ሰዎች ሁሉ ወደ እኔ ኑ ከፍሬዬም ትጠግባላችሁ፡፡ 

20. ስም አጠራሬ ከማር፣ ርስትነቴም ከሸንኮር ይልቅ ይጣፍታልና፤

21. የሚመገቡኝም አይጠግቡኝም፣ የሚጠጡኝም አይሰለቹኝም፤ 

22. የሚሰማኝም አያፍርም፣ ለእኔ የሚገዙ ሰዎች አይስቱም 

23. ይህ ሁሉ ነገር የልዑል የህጉ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ያዕቆብም ወገኖች ርስት ሙሴ ያዘዘበት ህግ ነው፡፡ 

24. በእግዚአብሔር የሚጸና አይደክምም እርሱ ያጸናችሁ ዘንድ ተከተሉት ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሐየር ብቻ ነው፡፡ ከእርሱም በቀር ሌላ አዳኝ የለም፡፡ 

25. ጥብን እንደ ኤፌሶን ፈሳሽ በሚያዝያም ወራት እንደሚመላ እንደ ጤግሮስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው፡፡

26. ምክርንም እንደ ኤፍራጥስ ፈሳሽ በአዝመራም ወራት እንደዮርዳኖስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው፡፡ 

27. ጥበብን እንደብርሃን በወይን አዝመራ ወራትም እንደአባይ ፈሳሽ የሚገልጣት እርሱ ነው፡፡ 

28. የመጀመሪያው አላወቃትም የመጨረሻውም ፍለጋዋን አላገኘም፤ 

29. ምስጢሯ ከባህር ውሃም ይልቅ ይበዛል ምክሯም ከባህሩ ጥልቀት ይልቅ ይጠልቃል፡፡ 

30. ከወንዝ እንደሚፈስስ ውሃ ሆንሁ፤ እንደ መስኖ ውሃ ወደ ተክል ቦታ ገባሁ፡፡ 

31. እንዲሁም አልሁ የተክል ቦታዬን ላጠጣት፣ የጎመን ቦታዬን ላጠጣት፣ ፈፋዬ እንደ ወንዝ ሆነልኝ ወንዜም እንደባህር ሆነልኝ፡፡ 

32. ዳግመኛም ጥበብን እንደጠዋት አበራታለሁ፤ እስከ ሩቅም ድረስ ብርሃኗን አሳያለሁ፡፡ 

33. ትምህርትን እንደ ትንቢት አፈስሳታለሁ፤ ለዘላለምም ለልጅ ልጅ አጸናታለሁ፡፡ 

34. እነሆ የደከምሁ ለሚፈልጉኝ ሰዎች ሁሉ ነው እንጂ ለእኔ ብቻ እንዳይደል እዩ፡፡