Sunday, October 6, 2013

ምዕራፍ ፵፰



ነብዩ ኤልያስ 
፩ ነቢዩ ኤልያስም እንደ እሳት ተነሳ ቃሉም እንደ ነበልባል ያቃጥል ነበር:: 
፪ ረኃብንም አመጣባቸው በቅንዓቱም አሳነሳቸው ::
፫ በእግዚአብሔርም ቃል ሰማይን ዘጋው ከሰማይም እሳትን ሦስት ጊዜ አወረደ:: 
፬ ኤልያስ ሆይ በታእምራትህ እንዴት ከበርህ እንዳንተስ የተመካ ማንነው? 
፭ በልዑል ቃል ከሞቱ ሰዋች ለይቶ ሞትን ከመቃብር ያስነሣ ማንነው?
፮ ነገሥታቱን ወደ ሞት የከበሩ ሰዎቹንም ከአልጋቸው ያወረዳቸው ማንነው? 
፯ በሲና የእግዚአብሔርን ተግሣጽ በኮሬብም የበቀልን ፍርድ የስማ ማንነው?
፰ ይበቀሉ ዘንድ ነገሥታቱን ከእርሱም ቀጥሎ ይተኩ ዘንድ ነቢያትን የቀባቸው ማንነው?
፱ በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረስ ወደ ሰማይ የወጣ ማንነው?
፲ መቅሠፍቱ ከመውረዱ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመልስ ዘንድ የአባትንም ልብ ወደ ልጅ ይመልስ ዘንድ የያዕቆብንም ወገኖች ያጻናቸው ዘንድ በተወሰነ ዘመን የተጻፈለት ማንነው? 
፲፩ የሚያውቁህና በፍቅርህ ያጌጡ ሰዎች ብፁዓን ናቸው እኛም ስለ አንተ በህይወት እንኖራለን :: 
ነብዩ ኤልሳዕ 
፲፪ በእሳት ሰረገላ ወደ ላይ የወጣ ኤልያስ ነው ከእርሱም መንፈስ የተመላ ኤልሳዕ ነበር በዘመኑም አለቆች አላስደነገጡትም ማንም እርሱን የተቋቋመው አልነበረም :: 
፲፫ ከነገሩም ሁሉም የተሳነው አልነበረም ከሞተ በኋላ በድኑ ትንቢትን ተናገረ :: 
፲፬ በሕይወቱም ሳለ ድንቅ ተአምራትን አደረገ በሞቱም ሥራው ድንቅ ነበረ :: 
፲፭ ከዚህም ሁሉ ጋር ሕዝቡ ንስሓ አልገቡም ከሀገራቸውም ተማርከው እስኪሄዱ ድረስ ኅጢአታቸውን አልተውም በሀገሩም ሁሉ ተበተኑ ከህዝቡም ጥቂት ሰዎች ቀረ::
፲፮ ከእነርሱም ደግ ስራ የሰሩ ነበሩ ኅጢአትም ያበዟት ነበሩ 
ንጉሡ ሕዝቅያስ
፲፯ ሕዝቅያስም ከተማውን አጸና በመካከልዋም ውኃን አስገባ ዓለቱንም በብረት ቁፈረ የውኃ መስኖ አሠራ 
፲፰ ስናክሬምም በዘመኑ ዘመተ ራፋስቂስንም ላከው ወደ እርሱም ሄዶ በጽዮን ላይ እጁን አነሣ ታበየ አፉንም ከፍ ከፍ አድርጎ ተናገረ ::  
፲፱ ያን ጊዜ ልቦናቸው ደነገጠባቸው እጃቸውም ዛለ እንደምትወልድ ሴትም ምጥ ያዛቸው ::
፳ ይቅር ባይ እግዚያብሔርንም ለመኑት እጃቸውንም ወደ እርሱ አነሱ ቅዱሱም ከሰማይ ፈጥኖ ሰማቸው በኢሳይያስም እጅ አዳናቸው ::
፳፩ የአሦርንም ሠራዊት አጠፋ መላኩም አጠፋቸው :: 
፳፪ ሕዝቅያስ እግዚያብሔርን ደስ የሚያሰኝው ሥራ ሠርቷልና በራእዪ ታላቅና ታማኝ የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስም እንዳዘዘው የአባቱ የዳዊትን መንገድ አጽንቷልና ::   
፳፫ ፅሐይም በዘመኑ ከመሄድ ወደ ኋላ ተመልሳለች የንጉሡም ዘመን ጨመረለት :: በታላቅ መንፈስ በመጨረሻ የሚሆነውን አየ በፅዮን የሚያለቅሱትንም አጽናናቸው :: 
፳፬ ለዘላለሙ የሚሆነውን የተሰወረውንም ሳይሆን ተናገረ ::