Sunday, October 6, 2013

ምዕራፍ ፵፭




፩፤ ስም አጠራሩ የከበረ የመላእክትም ብርሃን መልኩና ስም አጠራሩ የሆነ ሙሴ ደግ ነው እናመስግነው።
፪፤ አገነነው በጠላቶቹም ላይ የሚያስፈራ ሆነ።
፫፤ በቃሉም ተአምር አደረገ በነገሥታትም ፊት ተመሰገነ ስለወገኖቹም አዘዘው ብርሃኑንም አሳየው።
፬፤ ስለ የዋህነቱና ስለ ሃይማኖቱም አከበረው ከሰውም ሁሉ እሱን መረጠው።
፭፤ ወደ ብራሃን መጋረጃ አግብቶ ቃሉንም አሰማው ትዕዛዙንን በፊቱ ሰጠው ፤ለሁለቱ ነገድ አምልኮቱን ላሥሩ ነገድ ዘጠኙን ሕግጋት ያስተምራቸው ዘንድ የኦሪትንም ሕግ አስተማረው። 
፮፤ ከሌዊ ወገን የተወለደ ታላቅ ወንድሙ አሮንን እንደሱ የከበረ ነው እናመስግነው። 
፯፤ ፈጣሪውም ዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር ሕገ ኦሪት አጸናለት ሕዝቡ የለዩት አሥራቱንም ሰጠው፤ባማረ ጌጥም አስደነቀው የክብር ልብሱንም አለበሰው። 
፰፤ በሁሉም ዘንድ አስመካው መቅሠፍት በታዘዘበት ወራትም አጸናው እጀ ሰፊና እጀ ጠባብንም ኤፉድንም አለበሰው።
፱፤ በዙርያውም ብዙ የሆነ የወርቅ ጸናጽልና አበባ አለ በእግሩም በረገጠ ግዜ የመርገፉ ድምጽ ይሰማ ነበር ጮሆ የተናገረውም ነገር ቁምነገር ይሆን ነበር ለልጆቻቸውም ለወገኑም መታሰብያ ሆነ።
፲፤ የተለየ ሰማያዊ ሐር ያለበት አራት ኀብር አምስተኛ ወርቀ ዘቦ ያለበት በነጭ ሐር የተሰራ ልብስንም በሚገባና በውነት ነገር የተሰራ የሎግዮ ልብሱንም አለበሰው። 
፲፩፤ የነጭ ሐር የሚሆን ፈትሉ እጥፍ የሆነ የብልህ ሥራ የሚሆን ዋጋው ድንቅ የሆነ እንቁም ያለበት የማኀተምም ቅርጽ ያለበት ልብስን በልብስ ላይ አለበሰው እጀ ጠባቡም በወርቅ የተሠራ ነው ፤በየወገናቸው መታሰብያ ሊሆን በ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል ልጆች ቍጥር ልክ የተጻፈ ነው።
፲፪፤ በማኀተም መልክ አምሳል በተሠራ የተሰራ የወርቅ ቀጸላ በዝግባ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት የተለየ የክብሩመመክያ የሚሆን ታምራት የሚያደርግበት ሥራ የሚሆን ጌጡ ለዓይን የተወደደ የሆነ ጌጡ ፈጽሞ ያማረ የሆነ የወርቅ መጠምጠሚያን በዝግራ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት። 
፲፫፤ ከሱ አስቀድሞ ከሱም በኋላ እንደሱ ልብስ ያለ ልብስ አልተሰራም ከልጆቹ ብቻ በቀር ለዘለዓለሙ ከዘመዶቹም በቀር እንደሱ የለበሰ የለም። 
፲፬፤ ሁልጊዜ መስዋዕትን ይሰዉለት ዘንድ ዳግመኛም እየነጋ የማታና የጧት መስዋዕትን ይሰዉለት ዘንድ ልጆቹ ብቻ ዘመዶቹም ለበሱ እንጂ እንደሱ የለበሰ የለም። 
፲፭፤ ሙሴ እጃቸውን ቀባላቸው የተለየ ዘይትንም ቀባው ለዘለዓለሙ ሕግ ሆነው ይገዙለት ዘንድ አገልጋዮችም ይሆኑት ዘንድ ስሙን ጠርተው ሕዝቡንም ይባርኳቸው ዘንድ ሰማይ ጸንቶ በሚኖርበት ዘመን ልክ ለልጆቹም ሕግ ሆናቸው።
፲፮፤ ለእግዚአብሔር መስዋዕት ይሰዋ ዘንድ የበጎ መዓዛ መታሰብያ ሊሆን ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ለወገኖቹም ኃጢአታቸውን ያስተሠርይላቸው ዘንድ ከሰዎቹ ሁሉ እሱን መረጠ።
፲፯፤ ትዕዛዙን አስተማረው ለሁለቱ ወገን አምልኮቱን ያስተምራቸው ዘንድ ለዓስሩም ነገድ ዘጠኙን ሕግጋት ያስተምራቸው ዘንድ ዘጠኙን ሕግጋትና አምልኮትን ሠራለት።
፲፰፤ ልዩ የሆኑ ሰዎች ተከራከሩት የአቤሮንና የዳታን ወገኖች የሚሆኑ ሰዎች የነቆሬም ሠራዊቶች በምድረ በዳ ቀኑበት በጥፋትና በመቅሠፍትም ሞቱ።
፲፱፤ እግዚአብሔርም አይተው ደስ አላሰኙትም ተቆጥቶም አጠፋቸው በነሳቸውም ድንቅ ታምራት አደረገ በእሳትም አቃጠላቸው።
፳፤ ለአሮንም በክብር ላይክብር ጨመረለት ከእህላቸው የለዩትን አሥራቱንም ሰጠው የወገኖቹን ምድር እንዳይካፈሉ ለሱ የሰጠውን ለልጆቹም የሰጣቸውን። 
፳፩፤ የእግዚአብሔርን መስዋዕት ይበሉ ዘንድ የሚያጠግባቸውን አሥራቱን አስቀድሞ ሰራላቸው።
፳፪፤ እድልህ ርስትህ አሥራቱ ነው ብሎታልና ከሕዝቡ ጋራ ርስትን አልወረሰም። 
፳፫፤ ለእግዚአብሔር አምልኮት ቀንቷልና ወገኖቹን ለማስተማር ሾሞታልና ሹመቱ ሦስተኛ የሚሆን የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም ደግ ነው እናመስግነው በልቡናው ቸርነት ከእግዚአብሔር ፍቃድ የተነሳ ለእስራኤል ተገለጠ።
፳፬፤ በሙሴና በአሮን ሥራት ጸንቶ ሕዝቡን ያስተምራቸው ዘንድ ለልጆቹና ለሱም ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር ደግ ክህነት ገንዘብ ይሆናቸው ዘንድ።
፳፭፤ ከነገደ ይሁዳ ለተወለደ ለዳዊት ልጅም ጌጥ ይሆን ዘንድ በሕጉ ጸንቶ የሚኖር የልጁም መንግስትም እድል ይሆን ዘንድ ስለዚህ ነገር የፍቅር አንድነት መሐላን አጸናለት። 
፳፮፤ ከልቡናቸው ጥልቅ ብሎ የሚገባ ጥበብን ያስተምራቸ ው ዘንድ በዘመናቸው ሁሉ ክብራቸ ውና በረከታቸው እንዳይጠፉባቸው ወገኖቹንም በውነት ይገቧቸው ዘንድ ከልጆቹ ጋራ ለሱ ክህነት ርስቱ ነው።