Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፬




፩፤ ባፉ ያልተስነካከለ ሰው የተደነቀነ ነው። ኃጢአተኛ ሰውን ግን መንፈሳዊ ኃዘን አያስደነገጠውም።

፪፤ ኃጢአት ሠርቶ ሰውነቱን የሚያሳዝን አለኝታውንም የሚያጣ ሰው የተደነቀነ ነው። 

                    ሀብትን በሚገባ ስለ መጠቀም

፫፤ ነገር ለማያውቅ ሰው ሹመት አይገባውም፤ ለንፉግም ሰው ገንዘብ አይገባውም። 

፬፤ ሰውነቱን የሚነፍጋት ሰው ለሌላ ሰው ያከማቻል፤ ሌላ ሰው ግን በገንዘቡ ደስ ይለዋል።

፭፤ ሰውነቱን የሚነፍግ፥ በገንዘቡም ደስ የማይለው ሰው ለማን ይሰጥ ዘንድ አለው።

፮፤ ሰውነቱን ከሚነፍግ ሰው የሚከፋ የለም፤ ለክፋቱም እሱም ፍዳ ይሆነዋል። 
 
፯፤ በጎ ሥራም ቢያደርግ ባረጀ ጊዜ ብቻ ነው ኋላም ኃጢአቱ ይገለጣል።

፰፤ የንፉግ ሰው ዓይን ክፉ ነው፤ ከድሀ ፊቱን የሚመልስ ሰውነቱን ቸል ይላል። 

፱፤ ለስሱ ሰው ዓይን እድሉ አያጠግበውም፤ የልቦናውንም ንፍገት ሰውነቱን ያከሳዋል።

፲፤ የንፉግ ሰው ዓይኑ እህል ይነፍለጋል፥ በማዕድም ይነፍለጋል። 

፲፩፤ ልጄ፦ የሚቻልህን ያህል ሰውነትህን አዘጋጃት፣ በሚገባህ ገንዘብ ለእግዚአብሔር መባ አግባ።

፲፪፤ ሞት እንዳይቀር አስብ፥ የምትሞትባትም ቀን ትቀራለች ብለህ አትጠራጠር።

፲፫፤ ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ ነገር አድርግ፥ እጅህንም ዘርግተህ የተቻለህን ያህል ስጥ።
 
፲፬፤ በተድላህ፥ በደስታህ ጊዜ እንዳትታጣ ሁን፤ በጎ እድልም አያምልጥህ።

፲፭፤ ገንዘብህን ለባዕድ ትተዋለህና ወራሾችህ ገንዘብህን ሁሉ ይካፈላሉ። 

፲፮፤ ገንዘብህን አንሥተህ ስጥ፤ በመቃብር የምታገኝው፥ ተድላ ደስታ የለምና ሰውነትህን ደስ አሰኛት።

፲፯፤ ሕግ ቢያፈርሱ ሞት ተፈጥሯልና ሰው ሁሉ እንደ ልብስ ይጠፋል።

፲፰፤ ቅጠሉ ጭፍቅ ያለ፥ የእንጨት ቅጠል፣ የመጀመሪያው ቅጠል እንዲረግፍ ደማዊና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ እንዲሁ ነው፤ ይህ ይወልዳል ያ ይሞታል።

፲፱፤ ሥራው ሁሉ ፈጽሞ ይጠፋል፤ ሠሪውም ከሥራው ጋር ይጠፋል። 

                                    ጥበብን በመፈለግ የሚገኝ ደስታ
 
፳፤ ነገር ግን፥ ንስሐ ገብቶ የሞተው፣ ሕጉንም የጠበቀ፣ በገንዘቡም ያወቀበት ሰው የተደነቀነ ነው።

፳፩፤ የጥበብን ሥራዋን በልቡ የሚያስብ፥ ምሥጢሯንም የተማረ ሰው የተደነቀነ ነው።
 
፳፪፤ ጥበብን ተከተላት፥ ምሥጢሯንም መርምር ሥራቷንም ጠብቅ። 

፳፫፤ መስኮቷን የሚጐበኝ ባደባባይዎቿም ተቀምጦ የሚያዳምጥ። 

፳፬፤ በቤቷም አጠገብ የሚኖር፥ በዙሪያዋም የድንኳኑን ካስማ የሚተክል።

፳፭፤ ሰውነቱን በሥልጣኗ የሚያስጠብቅ፥ ባማረ ማደሪያዋም የሚኖር።

 ፳፮፤ ልጆቹንም በረድኤቷ የሚያስጠብቅ፥ በዘጠኙም ሕግጋት ጸንቶ የሚኖር። 

፳፯፤ በሷም ከመከራው የሚያርፍ፥ በክብሯም ጸንቶ የሚኖር ሰው የተደነቀነ ነው።