1 ልጄ ሆይ የበደልኸው በደል የሳትኸውም ነገር ቢኖር፣ እንዳትደግም
ተጠንቀቅ፣ ስለ ቀደመው ኀጢአትህም ንስሐ ግባ፡፡
2 ከክፉ አውሬ እንደሚሸሽ እንዲሁ ከኀጢአት ሽሽ፣ ካገኘችህ ግን
አትለቅህም፤ ጥርሷ እንደ አንበሳ ጥርስ ነው፤ የሰውንም ነፍስ ታጠፋለች፡፡
3 ሁለት አፍ እንዳለው የተሳለ ሰይፍ ኀጢአት ሁሉ እንዲሁ ናቸው፡፡
ካቆሰለችም ለቁስሏ ፈውስ የለውም፡፡
4 መመካትና
መኩራት፣ትዕቢትም ባለጸግነትን ያጠፏታል፤ እንደዚህም የትዕቢተኞችን ቤት ያጠፋሉ፡፡
5 ደሃ
በሚለምንበት ጊዜ አፉን አስከ ዦሮው ይከፍታል፤ ጩኸቱም ፈጥኖ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡
6 ምክርን
የሚጠላ ሰው ኀጢአተኞችን ይከተላቸዋል፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በመከሩት ጊዜ ልቡናውን ይመልሳል፡፡
7 ንግግርን
የሚችል ሰው ከሩቁ ይታወቃል፤ ለብልህ ሰውም የተሳተው ኀጢአቱ ይታወቀዋል፡፡
8 በብድር ገንዘብ ቤቱን የሚሠራ ሰው ሕንጻው እንደ ክረምት ግንብ ነው፡፡
9
የኀጢአተኞችም አንድነታቸው እንደ ገለባ ክምር ነው፤ ፍጻሜያቸውም ለእሳት ነበልባል ይሆናል፡፡
10
የኀጢአተኞች መንገድ ጐፃጒፅ ነው፡፡ መውጫዋም ገደል ነው፡፡
11 ልቡናውን ያጸና ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔርን
የመፍራትም መጨረሻዋ ጥበብ ነው፡፡
12 ያልተማረ ሰው ጠቢብ አይሆንም፤ ተምሮም ውርደት የሚበዛበት አለ፡፡
13 የብልህ
ሰው ዐሳቡ እንደ ክረምት ውኃ ብዙ ነው፤ ምክሩም እንደ ሕይወት ውኃ ይመነጫል፤
14 ያላዋቂ
ሰው ልብ እንደ ሰባራ ማድጋ ነው፤ የሰማውን ነገር ሁሉ መጠበቅ አይችልምና፡፡
15 አስተዋይ
ሰው የጥበብን ነገር በሰማ ጊዜ ያደንቃታል፤ ዳግመኛም በእርሱዋ ላይ ይጨምራል፤
16 የአላዋቂ
ሰው ነገሩ በራቀ ጎዳና እንዳለ እንደሚከብድ ሸክም ነው፤ የብልህ ሰው አንደበት መወደድ ግን መልካም ነው፡፡
18 ጥበብ በአላዋቂዎች ሰዎች ዘንድ እንደ ፈረሰች ቤት ናት፡፡ ያላዋቂ
ሰው ምክርም የማይወደድ ነገር ነው፡፡
19 ያላዋቂዎች ትምህርት እንደ ታሰረ እግር ነው፡፡ ያላዋቂዎች ልቡና ቀኝ
እጁን እንደ ታሰረ ሰው ደካማ ነው፡፡
20 አላዋቂ
ሰው በሳቀ ጊዜ ቃሉን ከፍ ያደርጋል፤ ብልህ ሰው ግን በጭንቅ ከንፈሩን ፈገግ ያደርጋል፡፡
21 ጥበብ
በአስተዋይ ሰው ዘንድ እንደ ወርቅ ጌጥ ናት፤ በቀኝ እጅ እንዳለ አምባርም ናት፡፡
22 ያላዋቂ
ሰው እግር ፈጥና ወደ ቤት ትገባለች፤ በትምህርት የተፈተነ ሰው ግን የሰውን ፊት ያፍራል፡፡
23 አላዋቂ
ሰው በደጃፍ ሆኖ የሰው ቤትን ይመለከታል፡፡ ዐዋቂ ሰው ግን በውጭ ይቆማል፡፡
24 ለሰው በበር ተጠግቶ ማዳመጥ አላዋቂነት ነው፤ በዐዋቂ ሰው ዘንድ ግን
ይህን ነገር ማድረግ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡
25 የለፍላፊ ከንፈር የማይመለከተውን ይናገራል፤ የጠቢባን ቃል ግን በሚዛን
የተመዘነች ናት፡፡
26 ያላዋቂዎች
ልባቸው ባፋቸው ነው፤ የአዋቂዎች አፍ ግን በልባቸው ነው፡፡
27 ኀጢአተኛ
ሰው ሰይጣንን ቢረግመው ራሱን መርገሙ ነው፡፡
28 ሐሜተኛ
ሰው ሰውነቱን ያረክሳል፤ ባደረበት ቦታ ራሱን ያስጠላል፡፡