Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፱




1 ሰካራም ሠራተኛ አይበለጥግም፣ ጥቂቱን የሚያቃልል ብዙውን ያጠፋል፡፡
 
2 መጠጥና ሴት ጠቢባንን ያስቷቸዋል፣ ጋለሞታን የሚከተላት በደለኛ ነው፡፡ 

3 የዚህም ፍጻሜው ትልና ጥፋት ነው፡፡ ደፋር ሰውነት ከመከራ አትጠበቅም፡፡

4 ፈጥኖ የሚያምን ልቡናው ቀሊል ነው፡፡ ኃጢአትን የሚሠራም ራሱን ይበድላል፡፡

5 ልቡናውን ደስ የሚያሰኝ ሰው ይደነቃል፡፡ 

6 ብዙ መናገርንም የሚጠላ ኀጢአቱን ያሳንሣል፡፡
  
7 የሰማኸውን ቃል አታውጣ፣ አትድገመውም፣ ለዘለዓለም የባሰ አያገኝህም፡፡

8 በወዳጅና በጠላት ዘንድ የምትናገረው ነገር አይኑር፣ ስተህ የሠራኸው ኀጢአትህንም አትንገር፡፡ 

9 ቢሰማ አይሰውርልህምና እስክትሞትም ድረስ ይጠብቀዋል፡፡ 

10 የሰማኸውን ቃል አታውጣ፣ ከዚህም በኋላ የሚያገኝህ ክፉ እንደሌለ እመን፡፡ 

11 አላዋቂ ሰው የሰማውን ነገር እስከሚያወጣ ድረስ ይቅበዘበዛል፡፡ ልጅ የምትወልድ ሴትም በምጥ እንደምትጨነቅ ይጨነቃል፡፡

12 የተወጋ ሰውም ጦሩን ከላዩ ይነቅል ዘንድ እንደሚቸኩል፣ አላዋቂ ሰው የሰማውን ቃል ያወጣ ዘንድ ይቸኩላል፡፡

13 ወዳጅህን አላደረገ እንደሆነ ወይም አድርጎ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው፡፡

14 ወዳጅህን፡- አልተናገረ እንደ እንደ ሆነ ወይም ተናግሮ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው፡፡

15 ወዳጅህን በጥላቻ ነገር ተሠርቶበት ይሆናልና ገሥጸው፤ ከልቡ ሳይፈቅድ የሚሳሳት ሰው አለና የነገሩህን ነገር ሁሉ አትመን፡፡

16 በአንደበቱ የማይሳሳት ማን ነው? 

17 ቁጣ ሳይበዛ ወዳጅህን ገሥጸው፣ ስለእግዚአብሔር ሕግም ቁጣን አሳልፋት፡፡ 

18 ጥበብ ሁላ እግዚአብሔርን መፍራት ናትና፣ ጥበብም ሁላ ሕጉን ታስጠብቃለችና፡፡ 

                       እውነተኛና ሐሰተኛ ጥበብ

19 ክፉን የሚያስተምር ጥበብ የለም፡፡ የኃጥአንም ምክር ጥበብ የላትም፡፡ 

20 ከሁሉ የምታረክስ ክፋት አለች፣ አእምሮ የጎደለው አላዋቂም አለ፡፡

21 ነገር ግን ከሚራቀቅ የእግዚአብሔርንም ሕግ ከሚክድ ይልቅ እግዚአብሔርን የሚፈራ አላዋቂ ይሻላል፡፡ 

22 እየበደለ የሚራቀቅና የሚጠነቀቅ አለ፣ ለባልንጀራው የሚያደላ ለወዳጁም ፍርድን የሚያቀና መስሎ ፍርድን የሚለውጥ ሰው አለ፡፡ 

23 እያመሰገነ ለክፉ ነገር የሚያደላ ሰው አለ፣ ልቡናው ግን ሽንገላ ተሞልቶአል፡፡

24 በልቡናው ሌላ ነገር እያለ ፊት አይቶ የሚያደላ አለ፣ ባላሰብኸውም ነገር ይመጣብሃል፡፡

25 ኀያሉ ቢደክም በአንተም ላይ ክፉ ማድረግ ቢሳነው፣ ያስትህ ዘንድ መከራን በግድ ያመጣብሃል፡፡

26 ሰው በመልኩ ይታወቃልና፣ ጠቢብም በገጹ ይታወቃል፡፡ 

27 ካለባበሱና ካካሄዱ ከአሳሣቁም የተነሣ የሰው ጠባዩ ይታወቃል፡፡