Sunday, October 6, 2013

ምዕራፍ ፴፩



ስለ ህልም ከንቱነት

፩.ሰነፍ ሰው ግን አሰተኛ ህልምን በከንቱ ተስፋ ያደርጋታል አሰተኛ ህልምም ሰነፍ ሰውን ያስደነግጠዋል 

፪. አሰተኛ ህልምን የሚያምን ሰው ጥላን እነደሚጨብጥ ነፋስንም እንደሚከተል ሰው ነው 

፫ ህልም ካለመሆን ወደ አለመሆን ይሔዳል በየምሳሌውም እየራሱ ያሳይሃል 

፬. ካህያ ምንም ምን መስዋት የሚሆን በግ አይወለድም ከሃሰተኛ ህልምስ እውነተኛ ነገር በየት ይገኛል፡፡

፭. ሐሰተኛ ህልም ጥንቆላ ሟርት ሁሉም ከንቱ ናቸው ልቡናንም ያስደነግጣሉ እንደምጥም ያጎብጣሉ፡፡ 

፮. ሐሰተኛ ህልም ብዙ ሰዎችን አስቷቸዋልና እሱንም ተስፋ እያደረጉ ጠፍተዋልና፡፡ 

፯. ይቅር ይል ዘንድ ከእግዚአብሔር የተገኘ ካልሆነ አሰተኛ ሕልምን በልብህ አታኑረው፡፡ 

፰. ያለ ሐሰትስ ከታየ በውነት ይደርሳል እውነተኛ ሕልምም የተረዳ ይሆናል፡፡

፱. የተማረ በመከራ የተገሰጸ ሰው ብዙ ምስጢር ያውቃል መከራን የተቀበለ ሰውም ጥበብን ያስተምራል፡፡ 

፲. በትምህርት ያልተነካ ሰው ግን የሚያውቀው ነገር የለም፡፡

፲፩. ብዙ መከራ የተቀበለ ሰው ብዙ ትምህርት ይማራል፡፡ 
 
፲፪. መከራ በተቀበልኩ ጊዜ ብዙ ምስጢር አየሁ አስቤ ከተውኩትም የተናገርሁት ነገር በዛ፡፡ 

፲፫. ለሞት እስክደርስ ጊዜ ድረስ ሁልጊዜ መከራ ተቀብያለሁና ስለዚህ ነገር፡፡

፲፬. እግዚአብሔር ከመከራ ያድነኛል፡፡ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሰውነት ከመከራው ትድናለች፡፡ 

፲፭. እሱን ያመኑ ሁሉ ይድናሉ 

፲፮. እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚያስፈራው የለም እሱ አለኝታው ነውና መከራ መጥቶበት አይደነግጥም፡፡

፲፯. እሱ ያድርበታልና የታመነ ወዳጁም ነውና፡፡ 

፲፰. እግዚአብሔርን የምትፈራ ሰውነት የተደነቀች ናት፡፡ 

፲፱. ኃይልነቱ የታመነ ነውና ረድኤቱም ጽኑ ነውና የእግዚአብሔር አይኖቹ የሚፈሩትን ሰዎች ይመለከታሉ በረሃውን ያቀዘቅዝልሃል ከቀትር ጸሃይም ይሰውርሃል ከመከራ ይጠብቅሃል ረድቶም ከመከራ ያድንሃል፡፡ 

፳. ሰውነትህን ያገናታል አይኖችህንም ያበራቸዋል ከደዌ ይፈውሳል ደኅንነትንም ይሰጣል በረከትንም ይሰጣል፡፡  

፳፩. የበደል መስዋት ተጠላ ነው ኃጢያተኞችም ቁርባናቸው አደፈኛ ነው፡፡ 

፳፪. ሕግ የዘነጉ ሰዎች መስዋዕትን አይቀበልም፡ 

፳፫. በመባህ ብዛት ኃጢአትህን የሚያስተሰርልይህ አይደለም፡፡ 

፳፬. ልጁን ባባቱ ፊት የሚገድለው ሰው ደስ እንዳያሰኝ ሰርቆ ቀምቶ መባ የሚያገባ ሰው እንደዚያ ደስ አያሰኝም፡፡ 

፳፭. የድሃ ህይወቱ ምጽዋት መለመን ነው፡፡ እምቢ ያለው ሰው ግን ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ 

፳፮. ባልንጀራውን ገደለ ሰው ደስ እንዳያሰኝ፤ ነገር ሰርቶ ባልና ሚስትንም የሚያፋታ ሰው የባልንጀራውን እንደገደለ ሰው ነው፡፡

፳፯. የምንደኛውን ደመወዝ የቀማ ሰው ደሙን ማፍሰሱ ነው፡፡

፳፰. አንዱ ሲሰራ አንዱ ቢያፈርስ የሁለቱስ ድካማቸው ምን ይጠቅማል፡፡  

፳፱. አንዱ ቢመርቅ አንዱ ቢረግም ከሁለቱ የማናቸውን ቃል ይሰማል፡፡

፴. ሬሳ ከዳሰሰ በኋላ እጁን ቢታጠብ ዳግመኛ ሬሳውን ከዳሰሰ የፊተኛው መታጠብ ምን ይጠቅመዋል፡፡

፴፩. ስለ ኃጢአቱ የሚጾም ሰው ዳግመኛ ይበድል ዘንድ ቢሄድ ከዚህ በኋላ ጸሎቱን ማን ይሰማዋል ሰውነቱንስ ማሳዘን ምን ይጠቅመዋል ፡፡