Saturday, October 5, 2013

ምዕራፍ ፲፮




፩፤ ጥቅም የሌላቸው ብዙ ልጆችን አትውደድ፥ በክፉ ልጆችም ደስ አይበልህ። 

፪፤ በነሳቸው እግዚአብሔር መፍራት ከሌለባቸው፥ ቢበዙም በነሳቸው ደስ አይበልህ። 

፫፤ በሕፃንነትም ሳሉ አትመናቸው፥ ብዛታቸውም ደስ አያሰኝህ። ከሺህ ልጆች አንድ አዋቂ ልጅ ይሻላል፥ ክፉ ልጅም ከመውለድ ሳይወልዱ መሞት ይሻላል።

፬፤ አዋቂ በሆነ ባንድ ልጅ አገር ትጸናለችና፥ በኃጢአተኞች ልጆች ብዛት ግን ጥፋት ትጠፋለችና፣ ክፉ ልጅ ከመውለድ ሳይወልዱ መሞት ይሻላል። 
 
፭፤ ዓይኔ እንዲህ ያለ ብዙ ነገሮች አየች። ከዚህም የሚበልጥ ዦሮዬ ሰማች። 

፮፤ በኃጢአተኞች ወገኖች መቅሠፍት ትመጣለች፥ በወንጀለኞችም ወገኖች ጥፋት ትመጣለች። 

፯፤ በኃይላቸው የታመኑ የቀደሙ አርበኞችም ሰውነታቸውን አላዳኑም።

፰፤ ሎጥ ለኖረባቸው ራሳቸውን ላኮሩ፥ ሎጥንም ላስጸየፉት አገሮች አልራራላቸውም።

፱፤ በኃጢአታቸው ጠፉ እንጂ፥ ኃጢአተኞች ወገኖችንም ይቅር አላላቸውም። 

፲፤ የተሰበሰቡ ልቦናቸውንም ያከፉ፥ እነዚህ ስሳ እልፍ አርበኞች ናቸው።

፲፩፤ ክሣደ ልቦናውን ያጸና አንድ ሰው ቢኖር እሱ ቢድን ድንቅ ነው፥ ይቅርታ መቅሠፍት ከሱ ዘንድ ይመጣልና፣ ይቅር ማለት ይችላል፤ መቅሠፍትንም ማምጣት ይችላል። 
 
፲፪፤ ቊጣውእንደ ቸርነቱ ብዛት መጠን ነው፥ ሰውንም እንደ ሥራው ይከፍለዋል።

፲፫፤ ኃጢአተኛ ሰው ከመከራ አያመልጥም፥ ደግ ሰውም የትዕግሥቱን ዋጋ አያጣም። 

፲፬፤ ምጽዋቱ ሁሉ ይቅርታን ያመጣል፥ ሰውም እንደ ሥራው ዋጋውን ያገኛል። 

፲፭፤ ኃጢአት ሠርተህ ከእግዚአብሔር አመልጣለሁ በሰማያትም የሚያገኘኝ የለም።

፲፮፤ በብዙ አሕዛብም ዘንድ የሚያውቀኝ የለም። 
 
፲፯፤ የሰውነቴስ ቊጥሯ ለዓለሙ ሁሉ ምንድ ነው አትበል።

፲፰፤ እነሆ፦ ይህ ሰማይ፥ ከሰማይም በላይ ያለ ሰማይ፣ ከሰማይም በታች ያለ ውቅያኖስ፣ ምድርም በመዓት በጐበኛቸው ጊዜ ሁሉ ያልፋሉ። 

፲፱፤ ተራሮችም፥ የምድርም መሠረት በመዓት ባያቸው ጊዜ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዋወጣሉ።

፳፤ ይህንንም ልብ አያስበውም፥ የእግዚአብሔርን ሥራውን ማን ያውቃል፣ ገናንነቱስ ጠንቅቆ ማን ያውቃል።

፳፩፤ ሰው የማያየው ፍጥረቱ ነፋስ ነው፤ ከሰው የተሠወረ፥ ፍጥረቱም ብዙ ነው። 

፳፪፤ እውነት ሥራ መሥራትን ማን ያሥተምራል፥ የይቅርታውንስ አለኝታ ማን ደጅ ይጠናል።

፳፫፤ አእምሮ የሌለው ሰው እንዲህ ያስባል፥ ሰነፍ በደለኛ ሰውም ስንፍናን ያስባል።

                        የእግዚያብሔር ጥበብ በሥነ ፍጥረት 

፳፬፤ ልጄ፦ ስማኝ፥ ጥበብንም ተማር፣ ነገሬንም ከልቦናህ አድምጠው።

፳፭፤ በልቦናህ መርምረህ ጥበብን ግለጣት፥ የትምህርትህንም ምሥጢሯን ተረዳ። 

፳፮፤ የእግዚአብሔር ፍጥረቱ፥ ለይኩን ባለው ቃሉ ተፈጠረ፤ በየወገናቸውም ሥራቸውን አየ።

፳፯፤ ይህ ዓለም፥ ጸንቶ በሚኖር ገንዘብ ሥራውን ሁሉ አዘጋጀ፣ ሠራዊታቸውንም በየወገናቸው አዘጋጀ፤ ይኸንን የፈጠራቸው እግዚአብሔር፥ አይራብም፣ አይጠማም። ብርሃናቸውም አይፈጸምም። 

፳፰፤ አንዱ ካንዱ ጋር አይጨናነቅም፥ ለዘለዓለሙ ከቃሉ አይወጡም።

 ፳፱፤ ከዚህ በኋላ፥ እግዚአብሔር ይህን ዓለም ጎበኘ፣ ዝናብንም አጠገበ።

 ፴፤ በደማዊት ነፍስ ሕያው የሆነ ፍጥረት ሁሉ በዚህ ዓለም መላ መመለሻቸውም ወደ መቃብር ነው።